ቀጥታ፡

በአማራ ክልል በተያዘው በጀት ዓመት ዳያስፖራውን ጨምሮ በክልሉ ከ3 ሺህ 700 የሚበልጡ ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ወስደዋል- የክልሉ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ

ባህር ዳር  ግንቦት 26/2015 (ኢዜአ) ፡- በአማራ ክልል በ2015 በጀት ዓመት ዳያስፖራውን ጨምሮ በክልሉ ከ432 ቢሊዮን ብር በላይ ያስመዘገቡ  ከ3 ሺህ 700 የሚበልጡ ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መውሰዳቸውን የክልሉ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ አስታወቀ።  

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ከክልሉ ጋር በመተባበር የዳያስፖራውን ተሳትፎ ማሳደግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ በእንጅባራ ከተማ አካሂዷል።


 

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ተፈሪ ታረቀኝ  እንደገለጹት ዳያስፖራው በኢንቨስትመንት ዘርፍ የሚያደርገውን ተሳትፎ ለማሳደግ ቀልጣፋ አገልግሎት እና አሰራር ለማመቻቸት ቢሮው ከአጋር አካላት ጋር በትብብር እየተሰራ ነው።

ዳያስፖራው ወደ ክልሉ መጥቶ በመረጠው የኢንቨስትመንት ዘርፍ እንዲሰማራ ያሉትን ፀጋዎች ለይቶ የማስተዋወቅ ስራ እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በተያዘው  ዓመት ብቻ ዳያስፖራውን ጨምሮ በክልሉ 432 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ  ከ3 ሺህ 700 የሚበልጡ ባለሃብቶች  የኢንቨስትመንት ፈቃድ መውሰዳቸው እና ከመካከላቸውም 86 ዳያስፖራዎች እንደሚገኙበት ጠቁመዋል።

ማኑፋክቸሪንግ፣አገልግሎት፣ትምህርት፣ጤና እና ግብርና ባለሀብቶቹ ፈቃድ ከወሰዱባቸው መስኮች መካከል  ጠቅሰዋል።

በሙሉ አቅማቸው ወደ ስራ ሲገቡ ለ780 ሺህ ዜጎች የስራ ዕድል ይፈጥራሉ ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ተወካይ አቶ መላኩ ዘለቀ በበኩላቸው ፤ አገልግሎቱ የዳያስፖራ ተሳትፎን ለማሳደግ ከባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ አሰራርን ለማጠናከር እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በዳያስፖራ የኢንቨስትመንት ተሳትፎ ላይ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን ለመለየትና መፍትሄዎች ለማበጀት ጥረት በማድረግ ላይ መሆኑን አመልክተዋል።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የዳያስፖራ ጉዳዮች አማካሪ አቶ አላዩ መኮንን በበኩላቸው፤ ዳያስፖራው ወደ ክልሉ መጥቶ መዋዕለ ንዋዩን በማፍሰስ የእውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲያደርግ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው ብለዋል።

ለዚህም ዳያስፖራው ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዘርፎች ላይ አተኩሮ እንዲሰራ የኢንቨስትመንት አማራጮች መለየታቸውን ገልጸዋል።

በእንጅባራ ከተማ በተካሄደው ውይይት ላይ ከፌዴራል፣ ከክልሉ እና ከሁሉም ዞኖች የተውጣጡ ኃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም