በ "ቡሳ ጎኖፋ" የመረዳዳት ባህል ሕዝቡ ከ16 ሺህ በላይ የቁም እንስሳትን በማሰባሰብ በድርቅ ለተጎዱ 8 ሺህ አባ ወራዎች ድጋፍ አድርጓል - ቡሳ ጎኖፋ ኦሮሚያ  

170

አዲስ አበባ ግንቦት 26/2015 (ኢዜአ) ፦ በ "ቡሳ ጎኖፋ" የመረዳዳት ባህል ሕዝቡ ከ16 ሺህ በላይ የቁም እንስሳትን በማሰባሰብ በድርቅ ለተጎዱ 8 ሺህ አባ ወራዎች ድጋፍ ማድረጉን ቡሳ ጎኖፋ ኦሮሚያ አስታወቀ። 

ድጋፉ ሕብረተሰቡ የተለያዩ የቁም እንስሳቶችን በባህሉ መሰረት በማሰብሰብ በድርቅ ተጎጂ የሆኑ አባ ወራዎች ከጉዳታቸው አገግመው ራሳቸውን እንዲችሉ ያደረገው በጎ ተግባር መሆኑም ተገልጿል፡፡  

የቡሳ ጎኖፋ ኦሮሚያ ምክትል ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ማሊቻ ሎጄ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በክልሉ 10 ዞኖች ተፈጥሮ የነበረው ድርቅ በሕዝቡ እና በእንስሳት ላይ ጉዳት አድርሷል፡፡  

በመንግስት በኩል ድርቁን ለመቋቋም በተሰራው ስራ በድርቁ ሳቢያ ለተጎዱ 3 ነጥብ 9 ሚሊዮን ዜጎች ከ2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የምግብ እህል ድጋፍ መደረጉን አመልክተዋል። 

በሌላ በኩል የተለያዩ አካላት ድጋፍ ያደረጉት ከ180 ሺህ በላይ ኩንታል የምግብ እህል ለተጎጂዎች መሰራጨቱን ተናግረዋል።

አሁን ላይ በድርቅ ተጎጂ በነበሩ አካባቢዎች ላይ ዝናብ በመጣል ላይ መሆኑን ገልጸው፤ ተጎጂዎች ራሳቸውን እስኪችሉ ድረስ ድጋፍ ይደረጋል ነው ያሉት ዶክተር ማሊቻ።

ቡሳ ጎኖፋ የኦሮሞ ሕዝብ ከጥንት ጀምሮ ሰው ሰራሽም ይሁን ተፈጥሯዊ አደጋዎች ሲያጋጥሙት እርስ በርስ የሚረዳዳበት ስርዓት መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህ ባህል መሰረት ባለፉት ጊዜያት ሕብረተሰቡ ከ100 ሺህ ኩንታል በላይ እህል በማሰባሰብ ለቦረና፣ ባሌ፣ ጉጂ እና ሐረርጌ ዞኖች ለድርቅ ተጎጂዎች ማድረሳቸውን አስታውሰዋል።

በተጨማሪም ከ16 ሺህ በላይ የቁም እንስሳትን በማሰባሰብ ከ8 ሺህ በላይ ለሚሆኑ የድርቅ ተጎጂ አባ ወራዎች ድጋፍ ማድረጉን በመጥቀስ።

መንግስት ድርቅ በተከሰተባቸው አከባቢዎች ዘላቂ የሆኑ የልማት ፕሮጀክቶችን በማከናወን ላይ መሆኑን የገለጹት ኃላፊው፤ ለዚህም በርካታ ግድቦች ተገንብተው የዝናብ ውሃ መያዛቸውን ገልጸዋል።

በሌላ መልኩ ዝናብ መዝነቡን ተከትሎ አርሶ አደሩና ከፊል አርብቶ አደሩ ወደ ሰብል ልማት እንዲገባ በመንግስት በኩል የዘር፣ የትራክተር እና የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት ተደራሽ መደረጉን ተናግረዋል።

አርሶ አደሩም በሰብል ልማት ስራው ላይ ትኩረት በማድረግ በምግብ ዋስትና ራሱን ለመቻል በትኩረት እንዲሰራ ድጋፉ ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።

በቦረና ዞን ከ5 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ 18 የውሃ ግድቦች ግንባታ የተከናወነ ሲሆን በአካባቢው በዘነበው ዝናብም 12 ግድቦች ውሃ መያዛቸው ተጠቁሟል።

”ቡሳ ጎኖፋ” የገዳ ስርዓት አካልና የኦሮሞ ሕዝብ ጥንታዊ የመረዳጃ ስርዓት ሲሆን፤ የኦሮሞ ህዝብ ሰው ሰራሽም ይሁን ተፈጥሯዊ ችግር ሲያጋጥመው ችግሩን ለማለፍ እርስ በርስ የሚረዳዳበት ባህላዊ እሴት ነው። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም