በመዲናዋ የጎርፍ አደጋን ለመከላከል የፍሳሽ ማስተላለፊያ መስመሮች በደረቅ ቆሻሻ እንዳይዘጉ ሕብረተሰቡ በባለቤትነት መጠበቅ እንደሚገባው ተገለጸ

126

አዲስ አበባ ግንቦት 26/2015 (ኢዜአ)፡-  በአዲስ አበባ በመጪው ክረምት የጎርፍ አደጋን ለመከላከል የፍሳሽ ማስተላለፊያ መስመሮች በቆሻሻ እንዳይዘጉ ሕብረተሰቡ በባለቤትነት እንዲጠብቅ የከተማው ጽዳት አስተዳደር ኤጀንሲ ጥሪ አቀረበ።

በአዲስ አበባ አራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሰባት ሳንፎርድ ኢንተርናሽናል ትምህርት ቤት አካባቢ የፍሳሽ ማስተላለፊያ መስመሮችን የማጽዳት ከተማ አቀፍ የፅዳት ንቅናቄ መርሐ-ግብር ዛሬ ተካሄዷል።


 

"የከተማችን የፍሳሽ ማስተላለፊያ መስመሮች የውሃ መውረጃ እንጂ የቆሻሻ መጣያ አይደሉም!" በሚል መሪ ቃል የተጀመረው መርሃ ግብር ለቀጣይ ሶስት ወራት እንደሚቆይ ተገልጿል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ታረቀኝ ወርቅነህ፤ አካባቢን ማፅዳት ብቻ ሳይሆን ዳግም የቆሻሻ መጣያ ቦታ እንዳይሆኑ ነዋሪው በባለቤትነት መጠበቅ እንዳለበት ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ ፅዳት በመጠበቅ ረገድ ማህበረሰቡ የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ጠይቀዋል።

የአዲስ አበባ ጽዳት አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር እሸቱ ለማ፤ በውሃ ማፍሰሻ ቱቦዎች በሕገወጥ መንገድ የሚጣሉ ቆሻሻዎች የጎርፍ አደጋ እንዲከሰት እያደረጉ ነው ብለዋል።

ሕብረተሰቡ በዚህ የፅዳት ንቅናቄ በሁሉም የመዲናዋ አካባቢዎች የሚገኙ የፍሳሽ ማስወገጃ መስመሮችን በባለቤትነት በማፅዳት በመጪው ክረምት ሊፈጠር የሚችል የጎርፍ አደጋን በመከላከል ረገድ የበኩሉን መወጣት እንደሚገባ ገልጸዋል።

ቆሻሻን በግዴለሽነት በየቦታው የሚጥሉ ግለሰቦችንና ድርጅቶችን ተጠያቂ ለማድረግ የአሰራር ደንብ መሻሻሉንም ነው ዶክተር እሸቱ ያመለከቱት።

 የአራዳ ክፍለ ከተማ የጽዳት አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ለምለም ንጉሴ  በክፍለ ከተማው  ካለፈው ሳምንት ጀምሮ እየተካሄደ ባለው የውሃ መውረጃ ቱቦዎችን ከደረቅ ቆሻሻ የማጽዳት ንቅናቄ 15 ሺህ ነዋሪዎች ተሳታፊ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

በጽዳት መርሐ ግብሩ በየሳምንቱ በቋሚነት በጎ ፈቃደኞች እና የብሎክ ነዋሪዎች እየተሳተፉ መሆኑንም አመልክተዋል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም