የቀቤና ብሄረሰብ የባህል ማዕከል ተመረቀ

 

ወልቂጤ ግንቦት 26 /2015 (ኢዜአ)፦ በቀቤና ልማት ማህበር በወልቂጤ ከተማ የተገነባው የቀቤና ባህል ማዕከል በደማቅ ሥነ ስርዓት ተመረቀ።

በስነ-ስርዓቱ ላይ የደቡብ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፋጤ ስርሞሎን ጨምሮ የፌደራልና የክልል ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።

በተጨማሪም የደቡብ ክልል የተለያዩ ብሔረሰቦች፣ የኦሮሚያ፣ የሲዳማ እና የሐረሪ ክልሎች እንዲሁም የአገር ሽማግሌዎች ተገኝተዋል። 
 

የቀቤና ልማት ማህበር የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ከማል ሱልጣን እንደገለጹት፤ የባህል ማዕከሉ የብሔረሰቡን ባህል፣ ታሪክና ቋንቋ ጠብቆ ለማቆየት ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል።

ማዕከሉ ሙዚየም፣ ቤተ መጽሐፍት እና የመሰብሰቢያ አዳራሾች እንዳሉት ገልፀው፤ ትውልዱ ነባር እሴቶችን እንዲያውቅ የሚያስችል ቅርሶችን የያዘ መሆኑን አመልክተዋል።

የልማት ማህበሩ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችሉ ተግባራትን ከመንግስት ጋር ተቀራርቦ እየሰራ እንደሆነ ጠቅሰው፤ በቀጣይ የተለያዩ የልማት ስራዎችን ለመስራት የሚያስችል ስትራቴጂካዊ ዕቅድ መንደፉን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም