የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ጥበቃና ድጋፍ ረቂቅ አዋጅ ዙሪያ የምክክር መድረክ እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ ግንቦት 26/2015 (ኢዜአ) የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ጥበቃና ድጋፍ ረቂቅ አዋጅ ዙሪያ ግብዓት ማሰባሰብ ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ነው።

የምክክር መድረኩ በሰላም ሚኒስቴር፣ በፍትሕ ሚኒስቴር፣ በዓለም አቀፉ ፍልሰተኞች ድርጅት እና በተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ኤጀንሲ ትብብር ተዘጋጅቷል።

በመድረኩ የሰብዓዊ መብት ተቋማት፣ የሲቪል ማህበራት፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ተወካዮችና ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል።


 

የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ስዩም መስፍን በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ ባለፉት ዓመታት በሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋ እናቶችና ህፃናትን ጨምሮ በርካታ ዜጎች ተፈናቅለዋል።

በኢትዮጵያ እስካሁን ለሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች የተሟላ ድጋፍ ማድረግ የሚያስችል የህግ ማዕቀፍ እንዳልነበረ አንስተዋል። 

በዝግጅት ሂደት ላይ የሚገኘው የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ጥበቃና ድጋፍ ረቂቅ አዋጅም ሰብዓዊ እርዳታ፣ የመብት ጥበቃን ጨምሮ ሌሎችም ድጋፎች እንዲደረጉላቸው እንደሚረዳ ጠቅሰዋል።

በዓለም አቀፍ ተሞክሮ መንግስታት ተፈናቃዮችን በተሟላ መልኩ ለመርዳት የአቅም ውስንነት ስለሚያጋጥማቸው የሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅቶችን እንደሚያሳትፉ ተናግረዋል።

በሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋ ምክንያት የሚከሰት የሀገር ውስጥ መፈናቀል በዜጎች ላይ የሚያሳርፈውን ዘርፈ ብዙ ጫና ለመቅረፍ ቅንጅታዊ የአሰራር ስርዓትን በህጋዊ አግባብ ለመምራትም ረቂቅ አዋጅ እየተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል። 

በረቂቅ አዋጁ መሰረት ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የሆነ ብሔራዊ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ጥበቃና ድጋፍ ምክር ቤት እንደሚቋቋም ተጠቁሟል።

ምክር ቤቱ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ ሆኖ የተለያዩ የመንግስት ተቋማትን፣ የኃይማኖት ተቋማትን፣ የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮችን እና እንደ አግባብነቱ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲካተቱ የሚደረጉ ሌሎች የሚመለከታቸው አካላትን ያቀፈ እንደሚሆን ተጠቁሟል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም