የሙስናና ብልሹ አሰራሮችን ለመታገል የጀመርነውን ጥረት እናጠናክራለን- በደቡብ ክልል የዘርፉ ባለሙያዎች

123

ሀዋሳ ግንቦት 26 /2015 (ኢዜአ)፡-  በተቋማት  ሙስናና ብልሹ አሰራሮችን ለመታገል   የጀመሩትን  ጥረት አጠናክረው  እንደሚቀጥሉ በደቡብ ክልል በተለያዩ ተቋማት የተመደቡ የጸረ ሙስና ክፍል ዳይሬክተሮችና ቡድን መሪዎች ገለጹ።

የክልሉ ስነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን በበኩሉ፤በየተቋማቱ ያሉ የጸረ ሙስናና ስነምግባር መከታተያ ክፍሎችን በአዲስ መልክ ለማደራጀት እየተሰራ መሆኑን ገልጿል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ  የሰጡ የተቋማት ዳይሬክተሮችና ቡድን መሪዎች፤  በተመደቡበት ተቋም የአሰራር ግድፈቶችን ለማስተካከል ከክልሉ ስነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ጋር በቅንጅት እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

በየተቋማቱ የሚታዩ ሙስናና ብልሹ አሰራሮችን በመታገልም እንደሃገር እየተከናወነ ላለው የጸረ ሙስና ትግል ንቅናቄ ውጤታማነት የድርሻቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።

የሃላባ ዞን ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን መምሪያ የስነ ምግባርና ጸረሙና ቡድን መሪ አቶ ተመስገን ሱዱኖ እንዳሉት፤  የሚሰሩበት ተቋም ለሙስና ተጋላጭ ከሆኑት ውስጥ ይጠቀሳል።


 

በተለይም ከመሬትና ገቢ አሰባሰብ ጋር ተያይዞ የሚታዩ ብልሹ አሰራሮች መኖራቸውን ጠቅሰው፤  ችግሩን የፈጠሩ ባለሙያዎችን ከቦታው ማንሳትን ጨምሮ የተለያዩ አስተዳደራዊ እርምጃ እንዲወስድ የሚጠበቅባቸውን መወጣታቸውን ተናግረዋል።

የደቡብ ክልል አርብቶ አደር ጉዳዮች ቢሮ የስነ ምግባርና ጸረ ሙስና ዳይሬክተር ወይዘሮ አበራሽ ኢሊጎ፤  መስኖን ጨምሮ በተለያዩ የአርብቶ አደር አካባቢዎች የልማት ፕሮጀክቶች የሚከናወንበት ተቋም መሆኑን  ገልጸዋል።

በዚህም ከዲዛይንና ግንባታ ጋር ተያይዞ ሊፈጠሩ የሚችሉ ክፍተቶችን በመከታተል ለሙስናና ብልሹ አሰራር ተጋላጭ እንዳይሆን በትኩረት እየሰራን ነው ብለዋል።

አርብቶ አደር አካባቢ በርካታ የልማት ጥያቄ መኖሩን ያነሱት ዳይሬክተሯ ፤ ለፕሮጀክት የተመደበው ገንዘብ በአግባቡ ስራ ላይ መዋሉን በመከታተል የህዝቡ ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ  ሃላፊነታቸውን እንደሚወጡ  ተናግረዋል።

ለሙስና ተጋላጭ በሆኑ ተቋማት አሰራሩን በየጊዜው መፈተሽና ለውጤታማነቱ የባለሙያዎችን አቅም ማጎልበትና ከለላ መስጠት እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል።

በመንግስት ተቋማት ውስጥ የስነ ምግባርና ጸረ ሙስና መከታተያ ክፍሎች መኖራቸው የሙስና ተጋላጭነታቸውን ይቀንሳል ያሉት ደግሞ የጋሞ ዞን ኢንቨስትመንት መምሪያ ስነ ምግባርና ጸረ ሙስና ቡድን መሪ አቶ ስንታየሁ ንጉሴ ናቸው።

በጸረ ሙስና ትግሉ ተገቢውን ለውጥ ማምጣት እንዲቻል የባለሙያዎችን አቅም ማጠናከር እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።

በተቋማት የተመደቡ ባለሙያዎችም ስለሚሰሩበት ተቋም ተገቢው እውቀት ኖሯቸውና ከሃላፊዎች ጋር በቅርበት ሰርተው እንደ ክልልም ሆነ እንደ ሃገር የተጣላባቸውን ሃላፊነት መወጣት አለባቸው ብለዋል።

የተመደቡበት ተቋም ከኢንቨስትመንት ጋር ተያይዞ ለሙስናና ብልሹ አሰራር ተጋላጭ የሚሆንበት እድል በመኖሩ ስራዎችን በቅርበት የመከታተል ሃላፊነታቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።


 

የደቡብ ክልል ስነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ አማኑኤል አብደላ በበኩላቸው፤ በክልሉ እየተከናወነ ባለው የጸረ ሙስና ትግል የተቋማት ስነ ምግባርና ጸረ ሙስና ዳይሬክተሮችና ቡድን መሪዎች ሚና ከፍተኛ ነው ብለዋል።

በዚህም ባለፉት ዘጠኝ ወራት በባለሙያዎች ክትትል በተከናወነው የቅድመ መከላከል ሥራ ከ293 ሚሊዮን ብር በላይ ሊመዘበር የነበረና የተመዘበረ ገንዘብ ብር ማዳን መቻሉን  ጠቁመዋል።

ይህንን ውጤታማ ተግባር ለማጠናከር በየተቋማቱ ያሉ የጸረ ሙስናና ስነምግባር መከታተያ ክፍሎችን በአዲስ መልክ የማደራጀት ተግባር  አቅጣጫ ተቀምጦ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

በዚህም በባለሙያ ደረጃ የነበረውን አደረጃጀት በክልል በዳይሬክተር፤  በዞንና ወረዳ ደግሞ በቡድን መሪዎች እንዲመራ መደረጉን ጠቅሰዋል ።

ተገቢ መረጃ ይዘው ሙስናና ብልሹ አሰራርን መከላከል እንዲችሉ በየተመደቡበትም ተቋም  የፊት አመራረነት ተሳትፎ እንዲኖራቸው መደረጉን ተናግረዋል።

 እንደ ሀገር አሳሰቢ  ደረጃ ላይ የደረሰውን የሙስናና ብልሹ አሰራሮች ለመከላከልና ለመቆጣጠር ግብረ ሀይል ተደራጅቶ በልዩ ትኩረት እየተሰራበት መሆኑ ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም