የክልል የፀረ-ሙስና ኮሚቴዎች የሙስና ወንጀል በፈጸሙ የመንግሥት አመራሮችና ሌሎች በርካታ ግለሰቦች ላይ ህጋዊ እርምጃ መወሰዱን ገለጹ

155

አዲስ አበባ ግንቦት 26/2015 (ኢዜአ)፡- በሀገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረውን የፀረ-ሙስና ትግል ለማጠናከር በየክልሉ የተሰየሙ የፀረ-ሙስና ኮሚቴዎች የሙስና ወንጀል በፈጸሙ የመንግሥት አመራሮችና ሌሎች በርካታ ግለሰቦች ላይ ህጋዊ እርምጃ መወሰዱን ገለጹ።

ኮሚቴዎች የምርመራና የተጠያቂነት ስራን በተጠናከረ መልኩ እያስቀጠሉ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

የሙስና ወንጀል በኢትዮጵያ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ተከትሎ መንግስት ሰባት አባላት ያሉት የጸረ- ሙስና ብሔራዊ ኮሚቴ በህዳር ወር 2015 ዓ.ም ማቋቋሙ ይታወቃል።

ይህንን ተከትሎ ክልሎችና ከተማ መስተዳደሮችም አምስት አባላት ያሉት ኮሚቴን በማቋቋም ሙስናን የመከላከልና ተጠያቂነትን የማስፈን ስራ እያከናወኑ መሆኑም እንዲሁ።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ የሲዳማ፣ የሃረሪና የጋምቤላ ክልል የስነ-ምግባርና ጸረ-ሙሰና ኮሚሽኖች  ኮሚቴው የሙስና ትግሉ እንዲፋጠን በማድረግ ረገድ የጎላ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይም ተጠያቂነትን በማረጋገጥና ፍትህን በማስፈን ረገድ ኮሚቴው የተቋቋመበትን ዓላማ በቁርጠኝነት እየተወጣ ስለመሆኑም ጠቁመዋል። 

የሲዳማ ክልል የስነ-ምግባርና ጸረ-ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘላለም ለማ፤ በክልሉ ሙስናን ለመከላከል፣ለመቆጣጠርና ተጠያቂነትን ለማስፈን እየተሰራ ነው ብለዋል።

የፀረ ሙስና ኮሚቴው መቋቋሙን ተከትሎም ህዝቡ በንቃት ጥቆማ የሚሰጥበትን አማራጭ በማስፋት በርካታ ጥቆማዎች እየመጡ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም እስካሁን የመጡ ጥቆማዎችን መነሻ በማድረግ በተካሄደ ምርመራና ክስ 136 ሰዎች ላይ ከአንድ ዓመት እስከ 11 ዓመት የሚደርስ የእስራት ቅጣት መተላለፉን ገልጸዋል።
 

የሃረሪ ክልል የስነ-ምግባርና ጸረ ሙሰና ኮሚሽን ኮሚሽነር ካሊድ ኑሪ በበኩላቸው፤ ኮሚሽኑ አባል የሆነበት  ኮሚቴ የሃብት ማስመዝገብና ማጣራት፣ በተቋማት ያሉ አሰራሮችን መፈተሽና ምርመራ ማካሄድ ተጠቃሽ ናቸው።

ለኮሚቴው እስካሁን የደረሱትን 67 ጥቆማዎች መሰረት በማድረግ 30 መዝገቦችን በመክፈት 11 በሚሆኑት መዝገቦች ላይ ምርመራ መጀመሩን አረጋግጠዋል።

በዚህም ወንጀል መፈጸማቻው በተረጋገጡ 25 የስራ ኃላፊዎችና ሙያተኞች ላይ እርምጃ መወሰዱን ገልጸዋል።
 

የጋምቤላ ክልል የስነ-ምግባርና ጸረ-ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ሳይመን ቶሪያል፤ ክልሉ በመሬት፣ በንግድና በነዳጅ ግብይት ከፍተኛ የሙስና ወንጀል እንደሚፈጸምበት ጠቅሰዋል።

በመሆኑም የፀረ ሙስና ኮሚቴ ተቋቁሞ በይበልጥ ለሙስና ተጋላጭ የሆኑ ዘርፎች ላይ የምርመራና የልየታ ስራ ከማካሄድ ጎን ለጎን ጥቆማዎችን መነሻ በማድረግ የምርመራ ስራ እያከናወነ ነው ብለዋል።

በተለይ በነዳጅ ግብይት ላይ ባደረገው ምርመራ 15 በርሜል ነዳጅ በህገ-ወጥ መልኩ ሊወጣ ሲል መያዙንና ወንጀለኞቹን ለህግ ማቅረብ መቻሉን ነው ኮሚሽነሩ ያስረዱት።

በክልሉ የነዳጅ ግብይቱ ላይ የአሰራር ማሻሻያ በማድረግ ረገድ ኮሚቴው የጎላ ሚና እንደነበረው አንስተዋል።

ህዝቡ ሙስናን በማጋለጥ ረገድ የጀመረውን የጥቆማ መስጠት ተግባር አጠናክሮ እንዲቀጥል ኮሚሽነሮቹ ጠይቀዋል።  

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም