በመዲናዋ ባለቤት አልባ ውሾች ለሰውና ለእንስሳት ጤና እክል እየፈጠሩ መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ ግንቦት 26/2015 (ኢዜአ) ፦ በአዲስ አበባ ባለቤት አልባ ውሾች እየተበራከቱና በሰውና በእንስሳት ላይ የጤና እክል እያደረሱ እንደሚገኝ ተገለጸ።

የእብድ ውሻ በሽታ (ሬቢስ) በቀላሉ ወደ ሰው የሚተላለፍና ገዳይ በሽታ ሲሆን መድኃኒትም እንደሌለው መረጃዎች ይጠቁማሉ ።

በሽታው ከውሻ ወደ ሰው  የሚተላለፍ ሲሆን  በወቅቱ ሕክምና ካልተደረገለት ለሞት የሚዳርግ ነው።

በሽታው የመከላከያ ክትባት እንዳለው ቢነገርም በመዲናዋ ካሉት ውሾች ብዛት አንጻር ክትባት የመስጠቱ ስራ በተፈለገው ልክ ተደራሽ እንዳልሆነም ይገለጻል፡፡

በአዲስ አበባ ባለቤት አልባ ውሾች መበራከታቸውን ተከትሎ በሰውና በእንስሳት ከፍተኛ የጤና እክል በማድረስ ላይ መሆናቸውን  ኢዜአ  ያነጋገራቸው  ታካሚዎችና የህክምና ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

ከታካሚዎቹ መካከል ምስላቸው እንዳይቀረጽ በመጠየቅ አስተያየታቸውን የሰጡት አቶ ቴዎድሮስ ሲሳይ በእብድ ውሻ ተነክሰው ሕክምና እየተከታተሉ መሆኑን ይናገራሉ።

ባለቤት አልባ ውሾች ከመንገድ ላይ ባለፈ በአንዳንድ ተቋማት አካባቢም መታየት መጀመራቸውን ጠቁመው  የሚመለከተው አካል ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ይላሉ።

ሌላው ታካሚ አቶ ደምስ መረጋ፤ በቀን ስራ የሚተዳደሩ ሲሆን ለስራ በሚንቀሳቀሱበት ወቅት በእብድ ውሻ እንደተነከሱ  ያነሳሉ።

ታካሚው ባላቸው የጤና መድህን መታወቂያ አደጋው እንደደረሰባቸው ለበሽታው ክትባት ማግኘት አለመቻላቸው እንዳሳዘናቸው ገልጸው በአሁኑ ወቅት ግን ሕክምናውን እየተከታተሉ መሆኑን ገልጸዋል።

በአፍንጮ በር ጤና ጣቢያ የጤና መድህን አገልግሎት ቡድን መሪ አቶ ታሪክ ተስፋዬ፤  ለእብድ ውሻ በሽታ ክትባት ለማግኘት በመዲናዋ ከሚገኙ 11 ጤና ጣቢያዎች ታካሚዎች ወደ ተቋሙ  እንደሚላኩ ገልጸዋል፡፡


 

በአሁኑ ወቅት የጤና መድህን አገልግሎት በጤና ጣቢያ ደረጃ አገልግሎት የሚሰጠው በተመዘገቡበት አካባቢ ብቻ መሆኑን አመልክተዋል።

በሆስፒታል ደረጃ ደግሞ በመረጃ ቋት የተሳሰረ ስርዓት ያለ በመሆኑ የጤና መድህን አባል የሆኑትን በመለየት  የእብድ ውሻ በሽታን ጨምሮ ሌሎች ሕክምናዎች በነጻ እንደሚሰጡ ጠቁመዋል።

የአፍንጮ በር ጤና ጣቢያ የድንገተኛ ሕክምና ክፍል ኃላፊ መቅደስ ኃይሉ የእብድ ውሻ በሽታ (ሬቢስ) ታካሚዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ይገልጻሉ።

በአብዛኛውም ተጎጂ እየሆኑ ያሉት ደግሞ የገቢ አቅማቸው አነስተኛ የሆኑና የጎዳና ተዳዳሪ ዜጎች መሆናቸውን አመልክተዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አርሶ አደርና ከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽን  ምክትል ኮሚሽነር ሙሰማ ጀማል፤ በበኩላቸው በመዲናዋ የሚገኙትን የባለቤት አልባ ውሾች ቁጥር ለመቀነስ ውሾችን እንዳይወልዱ የማምከንና የመከተብ ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል።


 

እስካሁን ባለው ሂደትም  በመዲናዋ ከ16 ሺህ በላይ ባለቤት አልባ ውሾችን መከተባቸውን ገልጸዋል፡፡

በተለየ መልኩ በመዲናዋ በሽታው በተከሰተባቸው አካባቢዎች ውሾችን የመከተብና ለጤና ስጋት አለመሆናቸውን የማረጋገጥ ስራ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

የመዲናዋ ነዋሪዎች ውሾቻቸውን በዓመት አንድ ጊዜ የማስከተብና የመንከባከብ ግዴታቸውን እንዲወጡ ምክትል ኮሚሽነሩ ጥሪ አቅርበዋል።

በአዲስ አበባ የእብድ ውሻ በሽታ ክትባት በሶስት ጤና ጣቢያዎች ብቻ እንደሚሰጥም መረጃዎች ያመለክታሉ።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም