በሐረሪ ክልል በበጀት ዓመቱ 10 ወራት ከ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ተሰበሰበ

166

ሐረር ግንቦት 26/2015(ኢዜአ)፡-  በሐረሪ ክልል በ2015 በጀት ዓመት 10 ወራት  ከተለያዩ  የገቢ ምንጮች ከ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር  በላይ መሰብሰቡን የክልሉ ገቢዎች ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ኃላፊ አቶ በቀለ ተመስገን ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በክልሉ የታቀደውን የልማት ስራ ለማሳካት  የገቢ አሰባሰብ ስርዓትን በማዘመን በኩል በትኩረት እየተሰራ ነው።

የልማት እቅዶቹን ለማሳካት ቢሮው በተለይ የአገልግሎት አሰጣጥን በማጎልበትና በቴክኖሎጂ የተደገፉ አሰራሮችን በማመቻቸት የገቢ አሰባሰብ ስርዓቱት ለማሳደግ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በክልሉ በበጀት ዓመቱ ያለፉት አስር ወራት ከቀጥታና ቀጥታ ካልሆነ ታክስ እንዲሁም ታክስ ነክ ካልሆነና ከማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ከ1 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ተሰብስቧል።

ይህም አፈጻጸሙ  ከእቅዱ በላይ እንደሆነና ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ደግሞ በ44 ነጥብ 6 በመቶ ብልጫ እንዳለው ነው የቢሮ ኃላፊው ያመለከቱት። 

ገቢው በብልጫ የተሰባሰበው በተለይም ከግብር አሰባሰብ ጋር በተያያዘ የአገልግሎት አሰጣጥ ስራዎች በማዘመን በደረሰኝ አቆራረጥ ላይ የተጠናከረ ክትትልና ቁጥጥር መደረጉ፣ውዝፍ ክፍያዎች በመሰብሰባቸውና ወደ ሕጋዊ ንግድ የሚገቡ ነጋዴዎች ቁጥር በመጨመሩ ነው ብለዋል።

እንዲሁም በክልሉ “ከየካቲት እስከ የካቲት” በሚል መሪ ሀሳብ የተጀመረው የግብር ንቅናቄ ለገቢው መጨመር አስተዋጽኦ ማድረጉን አስረድተዋል።

የሚሰበሰበው ገቢ የክልሉን ነዋሪ የልማት ጥያቄዎች ለመመለስ የሚከናወኑ  የልማት ስራዎችን እየደገፈ ይገኛል ነው ያሉት።

በበጀት ዓመቱ ቀሪ ወራት የክልሉ ገቢን ለማሳደግ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አቶ በቀለ ገልጸዋል።

ከክልሉ ግብር ከፋዮች መካከል በሸቀጣ ሸቀጥ ንግድ የተሰማሩ አቶ ጌታቸው ፍቅሩ በሰጡት አስተያየት፤ ግብር ካልተከፈለ ልማት የለም ብለዋል። 


 

ከዚህ ቀደም ግብርን ለመክፈል በቢሮው በኩል ይታዩ የነበሩ የአሰራር ክፍተቶች በአሁኑ ወቅት ተሻሽሎ  የተቀላጠፈ አገልግሎት እያገኙ እንደሚገኝ ገልጸዋል። 

በሐረር ከተማ በሆቴል ስራ የተሰማሩት አቶ ደሳለኝ አስፋው ለአገርና ለሕዝብ ልማት መሰረት የሆነውን ግብርን ሁሉም ዜጋ በተነሳሽነት በመክፈል ግዴታውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል። 


 

በሐረሪ ክልል ከ27 ሺህ  በላይ ግብር ከፋዮች እንዳሉ ከክልሉ ገቢዎች ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም