የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 27ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬም ቀጥለው ይካሄዳሉ

327

አዲስ አበባ ግንቦት 26/2015 (ኢዜአ) ፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 27ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር የሶስተኛ ቀን ውሎ ዛሬ ሁለት ጨዋታዎች በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይደረጋሉ።
በመርሃ ግብሩም ኢትዮጵያ መድን ከኢትዮጵያ ቡና ከቀኑ 7 ሰአት ላይ ይጫወታሉ።

በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ኢትዮጵያ መድን በ45 ነጥብ 3ኛ ሲሆን ኢትዮጵያ ቡና በ38 ነጥብ 4ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ኢትዮጵያ መድን በፕሪሚየር ሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ተከታታይ  ጨዋታዎች በሁለቱ አሸንፎ በሁለቱ ሲሸነፍ አንድ ጊዜ አቻ ወጥቷል።

ተጋጣሚው ኢትዮጵያ ቡና በአንጻሩ ካለፉት አምስት የሊጉ ጨዋታዎች ሁለቱን ሲያሸንፍ በአንዱ ተሸንፏል። ሁለት ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርቷል።

ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያ ዙር ባደረጉት ጨዋታ ኢትዮጵያ መድን 1 ለ 0 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።

በሌላኛው የ27ኛ ሳምንት የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ መርሐ-ግብር ወልቂጤ ከተማ ከፋሲል ከነማ ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

በደረጃ ሰንጠረዡ ወልቂጤ ከተማ በ32 ነጥብ 13ኛ ደረጃን የያዘ ሲሆን ፋሲል ከነማ በ37 ነጥብ 6ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ወልቂጤ ከተማ በፕሪሚየር ሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ተከታታይ  ጨዋታዎች በሁለቱ አሸንፎ በሁለቱ ተሸንፎ አንድ ጊዜ አቻ ወጥቷል።

ተጋጣሚው ፋሲል ከነማ በበኩሉ ባለፉት አምስት የሊጉ ጨዋታዎች ሁለት ጊዜ ሲያሸንፍ በተመሳሳይ ሁለት ጊዜ ሽንፈት ገጥሞታል። አንድ ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርቶ ወጥቷል።

ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያው ዙር ያደረጉት ጨዋታ ያለ ምንም ግብ በአቻ ውጤት መጠናቀቁ የሚታወስ ነው።

በተያያዘም ትናንት በተደረጉ የ27ኛ ሳምንት የሊጉ ጨዋታዎች ሃዋሳ ከተማ ወላይታ ድቻን 3 ለ 1 እንዲሁም አዳማ ከተማ  ድሬዳዋ ከተማን 2 ለ 1 አሸንፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም