የእምነት ቤቶች ክብር፤ ሰላምና ደህንነት እንዲጠበቅ ሁሉም ወገን የድርሻውን ሊወጣ ይገባል - የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ

208


አዲስ አበባ ግንቦት 25/2015 (ኢዜአ) ፦ የእምነት ቤቶች ክብር፤ ሰላምና ደህንነት እንዲጠበቅ ሁሉም ወገን የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ሲል የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ገለጸ።

የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ መግለጫ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል።


በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ ከተማ በአንዋር መስጅድ የጁምአ ሰላት ከተሰገደ በኋላ በሸገር ከተማ አስተዳደር ስለፈረሱ መስጅዶች ተቃውሞ ለማሰማት የተደረገውን ሙከራ ተከትሎ በተፈጠረው ግጭትና በተወሰደው የኃይል እርምጃ በሰዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰ እየወጡ ያሉ መረጃዎች ይጠቁማሉ።  


በተመሳሳይ ባለፈው ሳምንትም ግንቦት 18 ቀን 2015 ዓ.ም በአዲስ አበባ በታላቁ አንዋር እና በኑር (በኒን) መስጅዶች ከጁምአ ሰላት በኋላ በተፈጠረው ተቃውሞና በጸጥታ ኃይሉ የተወሰደው ያልተመጣጠነ እርምጃ ምክንያት ሁለት ሰዎች የሞቱ ሲሆን በርካታ ቁጥር ያላቸው ሙስሊሞችም ከባድና ቀላል አካላዊ ጉዳት ደርሶባቸዋል።


ስለሞቱት ወገኖቻችን ጉባኤው የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን እየገለፀ ለሟቾች ቤተሰቦች ወዳጅ ዘመዶች ሁሉ መጽናናትን ይመኛል፤ በተጨማሪም በዕለቱ የአካልና የሥነ ልቦና ጉዳት ለደረሰባቸው ሁሉ ፈጣን ፈውስን እንዲያገኙ ጉባኤያችን ልባዊ ምኞቱን ይገልፃል።


በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንም በምዕራብ ጎጃምና በአርሲ ሀገረ ስብከት በሚገኙ ሁለት አጥቢያዎች ላይ ደረሰ ስለተባለው ጉዳት እየተጣራ እንደሚገኝ የቤተ ክርስቲያኒቱ የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ በይፋዊ የፊስ ቡክ ገጹ ያወጣው መረጃ ይጠቁማል።


መስጅዶች እና አብያተ ክርስቲያናት የአማኞች የሃይማኖታዊ፣ የመንፈሳዊ እና የሞራላዊ ዕሴቶች የሚገነባባቸው ዋነኛ ማዕከላት ከመሆናቸውም በላይ የምዕመናን ልዩ ምልክቶች እንደሆኑ የሚታወቅ ሲሆን አማኞችም ከእምነት ተቋማትና ከቤተ እምነቶቻቸው ጋር ያላቸው መንፈሳዊና ስሜታዊ ትስስርም ጠንካራ ነው።


ከዚህ አንጻር በአዲሱ በሸገር ከተማ አስተዳደር በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ መስጅዶችና የእምነት ቤቶች ሕጋዊነት ጋር በተያያዘ በመፍረሳቸው ሙስሊሙን ህብረተሰብ አስቆጥቷል።


ከዚህ አንፃር ከመነሻው ጀምሮ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት ችግሩ በዘላቂነት እንዲፈታ ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ እንደቆየ የሚታወቅ ሲሆን በተለይም ባለፈው ሳምንት የደረሰውን ጉዳት ተከትሎ ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት በመስጠት ዘጠኝ አባላት ያሉት ኮሚቴ በማቋቋም ከመንግስት ጋር እየተነጋገር እንደሆነ መግለጫ በመስጠት የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳይ ከፍተኛ ምክር ቤት ሕዝበ ሙስሊሙ ዱአ እያደረገ በትዕግስት እንዲጠባበቅ ማሳሰቡ ይታወሳል።


ይሁን እንጅ መሪ ተቋሙ ያስተላለፈው ማሳሰቢያ እንደተጠበቀ ሆኖ በዛሬው እለት ማለትም ግንቦት 25 ቀን 2015 ዓ.ም ከጁምዓ ሰላት በኋላ ሁከትና አለመረጋጋት የተከሰተ ሲሆን የጸጥታ ኃይሉ በወሰደው እርምጃ ጉዳት መድረሱ በእጅጉ ያሳዝናል። 


ስለሆነም የሕዝበ ሙስሊሙ ብቸኛ መሪ ተቋም የሆነው የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ከመንግስት አካላት ጋር የጀመረው ውይይት እስኪጠናቀቅ ሕዝበ ሙስሊሙ በትዕግስት እንዲጠብቅ፣ በተመሳሳይ መንግስትም በተለይም የጸጥታ ኃይሉ የዜጎችን ሰላምና ደህንነት የማስጠበቅ ተግባሩን በከፍተኛ ጥንቃቄና ሆደ ሰፊነት እንዲያከናውን ጉባኤያችን በአጽንኦት እያሳስበ ሁሉም ወገን የመስጅዶችንና የቤተ እምነቶችን ክብር፣ ሰላምና ደህንነት በመጠበቅ የእምነት ቤቶች የተቋቋመበትን ዓላማና ተልዕኮ ለመፈጸም የሚቻልባቸው ቅዱስ ስፍራነታቸው የማክበርና የማስከበር ኃላፊነቱን እንዲወጣ እንጠይቃለን።


ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም