ከፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ-ኃይል የተሰጠ መግለጫ

239

ህዝበ ሙስሊሙ ለሀገራችን ሰላምና ደህንነት መረጋገጥ ጽኑ እምነት ያለው፣ ሀገር እየጠበቀ፣ እየገነባ እና የራሱን ድርሻ እያበረከተ መሆኑ ይታወቃል።

ሰሞኑን መስጅዶች ፈርሰዋል በሚል ምክንያት በተፈጠረው ሁከትና ብጥብጥ በሰው ህይወትና ንብረት ላይ ጉዳት የደረሰ ቢሆንም የፀጥታ አካላት የከፋ ጉዳት እንዳይደርስ መስዋዕትነት ከፍለው የከተማውን ሰላም ማረጋጋታቸው የሚታወቅ ነው።

ሌላ ተጨማሪ ጉዳት እንዳይደርስም የአዲስ አበባ ፖሊስ የከተማውን ሰላምና ደህንነት ለማወክ የሚንቀሳቀሱ ቡድኖች ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ በሰጠው መግለጫ ማሳሰቡ ይታወሳል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ግንቦት 25 ቀን 2015 ዓ.ም በአዲስ አበባ በሁሉም ክፍለ ከተሞች በሚገኙ መስጅዶች የተካሄደው የጁምአ ሶላት በሰላም ተጠናቋል።

የኢትዮጵያ እና የአዲስ አበባ ከተማ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤቶች ያስተላለፉትን ሰላማዊ መልዕክት በመተላለፍ በታላቁ አንዋር መስጅድ የጁምዓ ሶላት በሰላም ተጠናቆ ህዝብ ሙስሊሙ እየተመለሰ ባለበት ሁኔታ ሀይማኖትን ሽፋን በማድረግ ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለማፍረስ የሚንቀሳቀሱ የሴራ ቡድኖች የሰላቱን ሰላማዊ ሥነ-ሥርዓት ለማስከበር በተሰማሩ የፀጥታ አካላት ላይ ጉዳት ለማድረስ በተነሳ ረብሻ የሦስት ሰዎች ህይወት ሲያልፍ በተወሰኑ ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት ደርሷል። በንብረት ላይም እስከ አሁን ግምቱ ያልተወቀ ኪሳራ የደረሰ ሲሆን ለፀጥታ ሥራ በተሰማሩ 63 የፖሊስ አመራር እና አባላት ላይ ቀላል እና ከባድ የአካል ጉዳት የደረሰ መሆኑን የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ-ኃይል አስታውቋል።

ፀረ-ሰላም ኃይሎች የእምነቱ ተከታዮች በህጋዊ መንገድ ያቀረቡትን ጥያቄ በመጥለፍ የራሳቸውን እኩይ ዓላማ ለማሳካት ረብሻውን ወደ ሌሎች አካባቢዎች ለማዛመት ያደረጉት ጥረት የፀጥታ ኃይሉ፣ ህዝበ ሙስሊሙ እና የሀይማኖቱ አባቶች በጋራ በመሆን ባደረጉት ርብርብ መቆጣጠር ተችሏል፡፡

ግብረ-ኃይሉ የከተማውን ብሎም የሀገራችንን ሠላምና ደህንነት ለማስከበር የጀመረውን ህግ የማስከበር ሥራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል እየገለፀ የደረሰውን አጠቃላይ ጉዳት እና በህገ-ወጥ ተግባሩ ላይ የተሳተፉ ፀረ-ሰላም ኃይሎች ላይ የጀመረውን ምርመራ አጠናክሮ በመቀጠል በቀጣይ ውጤቱን ለህዝቡ ይፋ እንደሚያደርግ አስታውቋል።

ሰላም የሁሉም የእምነት ተቋማት የአስተምሮታቸው መሠረት በመሆኑ ህዝበ ሙስሊሙ የሚያነሳውን ማንኛውንም ጥያቄ በህግ አግባብ በሰላማዊ መንገድ ማስተናገድ የሚቻልበት ሥርዓት መኖሩን በመገንዘብ ለፀረ-ሠላም ኃይሎች መጠቀሚያ ሳይሆን የፀጥታ አካላት የከተማውን ሰላምና ደህንነት ለመጠበቅ የሚያደርጉትን ጥረት በመደገፍ ህዝበ ሙስሊሙ የዜግነት ድርሻውን እንዲወጣ የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ-ኃይሉ ጥሪውን ያቀርባል።

የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ-ኃይል

ግንቦት 25 ቀን 2015 ዓ.ም

አዲስ አበባ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም