የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ከኦራክል እና ቪዛ ኩባንያ ኃላፊዎች ጋር ተወያዩ

334

አዲስ አበባ ግንቦት 25/2015 (ኢዜአ):-የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶክተር) ከአሜሪካው ዓለም አቀፍ የኮምፒዩተር ቴክኖሎጂ ኦራክል ኩባንያ እና ከቪዛ የፋይናንስ አገልግሎት ኩባንያ ኃላፊዎች ጋር ውይይት አድርገዋል።

በሞሮኮ ማራካሽ ከግንቦት 23 ጀምሮ ሲካሄድ የቆየው ዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ አውደ ርዕይ(ጂአይቴክስ) ዛሬ ማምሻውን ተጠናቋል።

በአውደ ርዕዩ ላይ ከመላ ዓለም የተሰባሰቡ ታዋቂ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች እና ጀማሪ የቴክኖሎጂ ፈጣሪዎች የታደሙባቸው አውደ ርዕዮች እና አውደ ጥናቶች ተካሄደዋል።

በመድረኩ የተሳተፉት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶክተር) እና ልዑካናቸው ከመድረኩ አውደ-ርዕዮች እና የስማርት አፍሪካ አውደ ጥናት ተሳትፏቸው ጎን ለጎን ከተለያዩ ዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያ የስራ ኃላፊዎች ጋር ውይይቶችን አድርገዋል።

በአውደ ርዕዩ ማጠናቀቂያ ላይ ሚኒስትሩ ከኦራክል እና ከቪዛ ኩባንያዎች የስራ ኃላፊዎች ጋር ተወያይተዋል።

ዶክተር በለጠ በውይይቱ በኢትዮጵያ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ሂደት ላይ ማብራሪያ መስጠታቸውንና ኩባንያዎቹ በዲጂታላይዜሽን ስራዎች እና አገልግሎቶች ላይ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጥሪ ማቅረባቸው ተመላክቷል።

መንግስት ለዘርፉ እድገት አስቻይ ሁኔታዎችን ለመፍጠር እየሰራ እንደሚገኝ እና ለኩባንያዎቹ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም አስረድተዋል።

የኩባንያዎቹ ኃላፊዎች በበኩላቸው የኢትዮጵያ በዲጂታል ገበያ እድል ውስጥ ለመሳተፍ ፍላጎትና እቅድ እንዳላቸው መግለጻቸውን ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር  የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም