በአዲስ አበባ በተለያዩ ተቋማት የሚተከሉ 800 ሺህ የሚደርሱ ችግኞች ተዘጋጅተዋል - የጉለሌ እጽዋት ማዕከል

295

አዲስ አበባ ግንቦት 25/2015 (ኢዜአ)፦ ለዘንድሮው አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በአዲስ አበባ በተለያዩ ተቋማት የሚተከሉ 800 ሺህ የሚደርሱ ችግኞችን ማዘጋጀቱን የጉለሌ እጽዋት ማዕከል ገለጸ።

የጉለሌ ዕጽዋት ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጉተማ ሞረዳ ለኢዜአ እንደገለጹት በዘንድሮው ዓመት በአዲስ አበባ በተለያዩ ተቋማት የሚተከሉ 800 ሺህ ችግኞች ተዘጋጅተዋል።

በዚህም ችግኝ ለሚያፈሉና ለሚያቀርቡ ዜጎች የሥራ እድል በመፍጠር ወጣቶቹ ገቢያቸውን ማሳድጉን ነው የገለጹት።

ማዕከሉ ለዘንድሮው ዓመት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር አገር በቀል የሆኑ ለአፈርና የውሃ ጥበቃ፣ ለፍራፍሬና ለምግብነት የሚውሉ ጨምሮ አካባቢን ለማስዋብ የሚውሉ ችግኞችን አፍልቶ ማዘጋጀቱን ጠቁመዋል።

ማዕከሉ ችግኞችን ከማፍላት ጎን ለጎን ባሉት 705 ሄክታር መሬት ላይ በ2014 ዓ.ም ከተከላቸው ችግኞች ውስጥ 90 በመቶው መጽደቁን ገልጸዋል።

በአገር አቀፍ ደረጃ ባለፉት አራት ዓመታት በተካሄደው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር 25 ቢሊየን ችግኞች መተከላቸው ይታወሳል።

በዘንድሮም የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር 6 ነጥብ 5 ቢሊየን ችግኞች ለመትከል ዝግጅት መደረጉን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ መግለጻቸውም እንዲሁ።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም