ታዳሽ የኃይል አማራጮችን በመጠቀም የኤሌክትሪክ አገልግሎትን ለዜጎች ለማዳረስ እየተሰራ ነው-የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር

180

ሆሳዕና ግንቦት 25/2015 ( ኢዜአ )፡-  በኢትዮጵያ ያሉትን ታዳሽ  የኃይል አማራጮችን በመጠቀም ለዜጎች የኤሌክትሪክ አገልግሎትን ለማዳረስ  እየተሰራ መሆኑን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ገለጸ። 

በሚኒስቴሩ የኢነርጂ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ኢንጂነር ሱልጣን ወሊ እና ሌሎች የተቋሙ ከፍተኛ አመራሮች በሀድያ ዞን ግቤ ወረዳ ገሰጣ ኦዳዳ ቀበሌ እየተገነባ ያለውን የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ጎብኝተዋል።


 

ለሁሉም አካባቢ ከዋናው የኤሌክትሪክ መስመር(ግሪድ) አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ አመቺ ባልሆኑ አካባቢዎች ያሉ አቅሞች ላይ የተመሰረተ የታዳሽ ኃይል አማራጭን በመጠቀም የኤሌክትሪክ አገልግሎትን ተደራሽነት ለማስፋፋት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል።

ለዚህም በሀዲያ ዞን ጊዜ ወረዳ ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ በጀት እየተነገባ ያለው ኃይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ  ግንባታ ፕሮጀክት በማሳያነት ጠቅሰዋል።

ይህም ከ20 ኪሎ ዋት በላይ ኃይል የማመንጨት አቅም እንዳለው እና ከኃይል አቅርቦት ባሻገር ለግብርናና ለሌሎች የልማት አገልግሎቶች ፋይዳ እንዳለው ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ከ65 ሚሊዮን በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማያገኘው ሕዝብ አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ የታዳሽ ኃይል አማራጭን መጠቀም የመጀመሪያው አማራጭ መሆኑን ተናግረዋል።

ታዳሽ የኃይል አማራጭን በመጠቀም የዜጎችን የኤሌክትሪክ ፍላጎት ለማሟላት የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎችን በአገር ውስጥ መጠቀም የሚያስችል እድል አለ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው።

የውሃ እና የፀሐይ ኃይል የተፈጥሮ ፀጋዎች በመጠቀም ዜጎች የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲያገኙ ለማድረግ ይሰራል ብለዋል።

የሀድያ ዞን ውሃ  መስኖና ኢነርጂ መምሪያ ኃላፊ አቶ መለሰ ኃይሌ የታዳሽ ኃይል አማራጮችን መጠቀም  የዛፍ ጭፍጨፋን ለማስቆም እና የእናቶችን ጊዜ እና ጉልበት ለመቆጠብ ፋይዳ እንዳለው ገልጸዋል።


 

የዜጎችን የኤሌክትሪክ የኃይል  ፍላጎትና የአቅርቦት ውስንነትን  ችግርን በዘላቂነት ለመፍተት  ሚኒስቴሩ  ለቴክኖሎጂው የተሰጠው ትኩረት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

በአካባቢያቸው በኤሌክትሪክ አገልግሎት ተደራሽነት ችግር  ተማሪዎች ኩራዝን በመጠቀም ትምህርታቸውን ተከታትለው አመርቂ ውጤት ለማምጣት ምቹ ሁኔታ እንዳልነበረ የተናገሩት በግቤ ወረዳ  የገሰጣ ኦዳዳ ቀበሌ  አርሶ አደር ግርማ አላሮ ናቸው።

በሚኖሩበት ቀበሌ ያለምንም ጥቅም ከዓመት እስከ ዓመት የሚፈሰውን የ"ለመሬ" ወንዝን በመጠቀም በአካባቢያቸው የኤሌክትሪክ ኃይል  ተደራሽ እንዲሆን እየተደረገ ያለው ጥረት አስደሳች መሆኑን ገልጸዋል።


 

የኃይል ማመንጫው አገልግሎት እስከሚጀምር ድረስ በጉጉት እየጠበቁ እንደሚገኙም ተናግረዋል።

የአካባቢው ማህበረሰብ ከሁለት ወራት በኋላ ኤሌክትሪክ አገልግሎት እንደሚያገኝ ተገልጿል።

በመስክ ምልከታው ላይ የፌዴራል እና  የሀድያ ዞን ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም