በኢትዮጵያ የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ማደግ አለበት - የፌዴራል ፍትህና ህግ ኢንስቲትዩት

153

ደሴ ግንቦት 25/2015 (ኢዜአ )፡- በኢትዮጵያ የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ማደግ እንዳለበት የፌዴራል ፍትህና ህግ ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

ዘላቂ ሰላም፣ ሰብዓዊ መብትና በሀገራዊ ምክክሩ አበይት ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ጉባኤ በወሎ ዩኒቨርሲቲ እየተካሄደ ነው፡፡

በውይይቱ ላይ የፌዴራል የፍትህና ህግ ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ምትኩ ማዳ እንደገለጹት በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ በቅንጅት መስራት ያስፈልጋል፡፡

ኢንስቲትዩቱም የህግ የበላይነት በሁሉም አካባቢዎች እንዲረጋገጥ የፍትህ ዘርፉን በጥናት፣ በስልጠናና አቅም ግንባታ እየደገፈ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

አገራዊ ምክክሩ ውጤታማ ሆኖ በኢትዮጵያ አሰተማማኝ ሰላም እንዲሰፍን የተጀመረውን ጥረት እንደሚደግፉም አስረድተዋል።

የህግ የበላይነት ተረጋግጦ የዜጎች ሰብዓዊ መብት እንዲከበር፣ ፍትህ እንዲሰፍን የሁሉም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ መጎልበት አለበት ነው ያሉት።

የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር መንገሻ አየነ በበኩላቸው ዘላቂ ሰላም፣ አንድነትና ልማት እንዲረጋገጥ ዩኒቨርሲቲው የድርሻውን እየተወጣ  እንደሚገኝ አስረድተዋል።

ለዚህም የጋራ ባህልና እሴቶቻችን በማጎልበት፣ ምሁራን ለህብረተሰቡ ግንዛቤ እንዲፈጥሩና አገራዊ ምክክሩ አሳታፊ እንዲሆን ከፌዴራል ተቋማት ጋር ጭምር እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፊሎሶፊ መምህሩ ዶክተር ዳኛቸው አሰፋም እንዲሁ በዚህ ወቅት ሁሉም ህዝብ ከግል ጥቅሙ ይልቅ ሀገርን ማስቀደም አለበት ብለዋል።

''ሁሉም ዜጋ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም፣ አንድነትና ልማት በጋራ መረባረብ ይኖርበታል'' ያሉት ዶክተር ዳኛቸው ምሁራንም ህዝብና መንግስትን የሚያቀራርቡ ጥናቶችን ማካሄድ እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።

''በብሄራዊ ምክክሩ ጠቀሜታ ዙሪያ ለህዝቡ ግንዛቤ በመፍጠር የድርሻችንን መወጣት አለብን'' ነው ያሉት።

ከ10 በላይ የጥናት ስራዎች በሚቀርቡበት የውይይት መድረክ ላይ ከፍተኛ አመራሮች፣ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ ምሁራንና ሌሎችም እየተሳተፉ ነው፡፡

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም