በሚቀጥሉት አስር ቀናት የሚኖረው የእርጥበት ሁኔታ ለበልግና ለመኸር ሰብሎች አመቺ ሁኔታ ይፈጥራል - የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት 

265

አዲስ አበባ ግንቦት 25/2015 (ኢዜአ) በሚቀጥሉት አስር ቀናት የሚኖረው የእርጥበት ሁኔታ ለበልግና ለመኸር ሰብሎች እንዲሁም ቋሚ ተክሎች አመቺ ሁኔታ እንደሚፈጥር የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ገለጸ።

ኢንስቲትዩቱ ለኢዜአ በላከው መግለጫ በቀጣዩቹ አስር ቀናት በተለይም በምዕራብ አጋማሽ የአገሪቱ ክፍሎች ላይ የተስፋፋ የዝናብ መጠንና ሥርጭት ይኖረዋል ብሏል።

ይህም በአካባቢዎቹ ላይ እየተከናወነ ለሚገኘውና ለሚጠበቀው የግብርና እንቅስቃሴ በአብዛኛው መልካም ጎን የሚኖረው ሲሆን የሚኖረው የዕርጥበት ሁኔታም የአፈር ውስጥ እርጥበትን ከማሻሻል አንጻር በጎ ሚና የሚጫወት መሆኑም ተመላክቷል።

በእነዚህ ቀናት የሚኖረው የእርጥበት ሁኔታ በተለይም ለበልግና ለመኸር ሰብሎች እንዲሁም ቋሚ ተክሎችና የጓሮ አትክልቶች አመቺ ሁኔታ እንደሚፈጥር ነው የተገለጸው።

እየተስፋፋ የሚሄደው ዝናብ ሰጪ የሚቲዎሮሎጂ ገጽታ ቀደም ብለው የመኸር እርሻ እንቅስቃሴን ለጀመሩ አካባቢዎችም ጠቀሜታው ከፍተኛ መሆኑንም እንዲሁ።

የሚኖረው እርጥበትም ለአርብቶ አደሮችና ከፊል አርብቶ አደሮች ለግጦሽና የመጠጥ ውሃ አቅርቦትም የጎላ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ተጠቅሷል። 

እንዲያም ሆኖ በተወሰኑ አካባቢዎች ላይ ከሚጠበቀው ከባድ ዝናብ ጋር ተያይዞ የጎርፍ አደጋ ሊያጋጥም ስለሚችል ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አሳስቧል። 

  

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም