የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የብዝሃነት ሚኒስትር ጋር ተወያዩ

289


አዲስ አበባ ኢዜአ ግንቦት 25/2015(ኢዜአ):-የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የብዝሃነት ሚኒስትር ሼህ ናህያን ሙባረክ አል ናህያን ጋር ተወያይተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በጥር 2015 በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የስራ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት በአቡዳቢ የአገሪቱ መንግስት በሰጠው 17 ሺህ 682 ካሬ ሜትር ላይ እየተሰራ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መጎብኘታቸው ይታወቃል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ለተባበሩት አረብ ኤምሬቶች መንግስት ምስጋና ያቀረቡ ሲሆን የዋና የቤተ ክርስቲያኑ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ለጊዜው መገልገያ የሚሆን ቤተ ክርስቲያን ግንባታ እየተጠናቀቀ መሆኑንም በወቅቱ ገልጸው ነበር።

ብፁዕነታቸው በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች መዲና አቡዳቢ ለሚገነባው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ሕንጻ መሰረት ድንጋይ ለማኖር እንዲሁም የመቃረቢያ ቤተ ክርስቲያን መርቀው ለመክፈት ትናንት ዩኤኢ መግባታቸው ይታወቃል።

አቡነ ማትያስ ዛሬ ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የብዝሃነት ሚኒስትር ሼህ ናህያን ሙባረክ አል ናህያን ጋር ውይይት አድርገዋል።


 

ሼህ አል ናህያን ቅዱስ ፓትርያርኩ ለጉብኝት ወደ አቡዳቢ በመምጣታቸው ክብር እና ደስታ እንደተሰማቸው ገልጸው ጉብኝታቸው በኢትዮጵያና በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች መካከል ያለውን የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ለማጠናከር አዎንታዊ ሚና ይጫወታል ብለዋል። 

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በበኩላቸው የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች መንግስት ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ሕንጻ መገንቢያ ለሰጠው መሬት ምስጋና ያቀረቡ ሲሆን ለተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ሕዝብ እና መሪዎች ጤናና ብልጽግናን ተመኝተዋል:: 
ከውይይቱ በኃላ የብዝሃነት ሚኒስትሩ ለቅዱስነታቸው እና ለልዑካን ቡድናቸው የምሳ ግብዣ አድርገዋል።


 

በስነ ስርዓቱ ላይ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የኢትዮጵያ አምባሳደር ኡመር ሁሴን እንዲሁም የበርካታ አገራት አምባሳደሮች እና የተለያዩ ቤተ እምነቶች ተወካዮች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም