በጎ አስተሳሰብ ይዞ ለአገር ግንባታ የሚተጋ ትውልድ ለመፍጠር ሁሉም የድርሻውን አስተዋጽኦ ሊያበረክት ይገባል- ዶክተር ፋንታ ማንደፍሮ

አዲስ አበባ ግንቦት 25/2015 (ኢዜአ):- በጎ አስተሳሰብ ይዞ ለአገር ግንባታ የሚተጋ ትውልድ ለመፍጠር ሁሉም የድርሻውን አስተዋጽኦ ሊያበረክት እንደሚገባ የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ፋንታ ማንደፍሮ ተናገሩ።     

ዓመታዊው አገር አቀፍ የመመሰጋገንና የመደናነቅ ቀን በሚሊኒየም አዳራሽ ተካሂዷል።

ቀኑ የትምህርት ሚኒስቴር፣ ሰላም ሚኒስቴር፣ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት እና ቅን ኢትዮጵያ ማህበር በጋራ ያዘጋጁት ሲሆን ተማሪዎች፣መምህራንና ወላጆች የሚመሰጋገኑበት መርሐ-ግብር ተካሂዷል።

በመርሐ-ግብሩ ላይ የሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ወላጆች እና ከተለያዩ ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ  ተማሪዎች ታድመዋል።

የዝግጅቱ ዓላማ በተለይም ምስጋናን ባህል ማድረግ፣ በትውልዱ ዘንድ ጥላቻንና መለያየት እንዳይኖር በትኩረት እንዲሰራበት ለማሳሰብ ያለመ መሆኑ ተገልጿል።  
 

በዚህ ዝግጅት ላይ ተማሪዎች መምህራኖቻቸውንና ወላጆቻቸውን የሚያመሰግኑበት ኪነ-ጥበባዊ ስራዎችና ልዩ ልዩ ዝግጅቶችን ቀርበዋል። 

የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ፋንታ ማንደፍሮ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ ትውልዱ ምስጋናንና መልካም ስነ-ምግባርን ባህል እንዲያደርግ የአስተማሪዎች፣ ወላጆች እና የትምህርት ዘርፉ ላይ ያሉ ባለድርሻ አካላት ድጋፍ ወሳኝ ነው ብለዋል።

የትምህርት ሚኒስቴር ከመደበኛ ትምህርት ጎን ለጎን ግብረ-ገብነት በተማሪዎች ዘንድ እንዲጎለብት በስርዓተ ትምህርት አካቶ እየሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።

ቀጣዩ ትውልድ አገር የሚገነባ እንዲሆን ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት በትብብር እየሰራ መሆኑን ገልጸው፤ ለተመሳሳይ ዓላማ መሳካት እየሰራ ካለው ቅን ኢትዮጵያ ማህበር ጋር በበርካታ ጉዳዮች ላይ በጋራ እየተሰራ እንደሆነ ተናግረዋል።   

የመምህራን አሻራ ያላረፈበት መሐንዲስ፣ ተመራማሪ እና ሳይንቲስት የለም ያሉት ሚኒስትር ደኤታው ለመምህራን ክብርና ምስጋና ብናቀርብ ሲያንስ እንጂ አይበዛም ሲሉ ገልጸዋል።      

እንደ ዶክተር ፋንታ ገለጻ መመሰጋገንና መደናነቅን ባህል የሚያደርግ ትውልድ ለመፍጠር ከታች ጀምሮ ትውልዱን ማነጽ ላይ ሊሰራ ይገባል ነው ያሉት።    
 

የሰላም ሚኒስትር ደኤታ ዶክተር ስዩም መስፍን በበኩላቸው "ምስጋና ለሰጪው የማይከብድ ለሚቀበለው ግን ከስጦታዎች ሁሉ የላቀ ዋጋ ያለው ስጦታ ነው" ሲሉ ገልጸዋል። 

ምስጋና አንድን ሰው የበለጠ የሚያተጋና የሚያነሳሳ አለፍ ሲልም ለዘላቂ እድገት መረጋገጥ አዎንታዊ ሚና ያለው መሆኑን አመልክተዋል።   

ሰላምን የሚያስቀድም ትውልድ በበጎ እይታ የሚመራ ትውልድ የመፍጠር ጉዳይ በአንድ ጀንበር የሚሳካ አይደለም ያሉት ዶክተር ስዩም ለዚህም ተከታታይ ሥራ ይፈልጋል ብለዋል።    
 

በዚህ ረገድም የመሰል የመመሰጋገን፣የመደናነቅና የመከባበር ሁነቶች  ትልቅ ሚና አለው ሲሉ ነው የገለጹት።

የቅን ኢትዮጵያ ማህበር መስራች ዶክተር ቶሎሳ ጉዲና እንደሚሉት፤ ማህበሩ በመልካም ስነ-ምግባር ታንጾ ለአገር ጠቃሚ ትውልድ የመፍጠር ዓላማን ለመደገፍ የተቋቋመ ነው።    

ማህበሩ በዚህ በኩል የድርሻውን እየተወጣ መሆኑን ገልጸው ወላጆች፣መምህራንና ሌሎችም የሚመለከታቸው አካላት የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት በላቀ ደረጃ እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

ጥላቻ፣ መለያየት፣ዘረኝነትና ክፋት በትውልዱ ዘንድ ቦታ እንዳይኖረው በማድረግ ረገድ የወላጆች ሚና ከፍ ያለ በመሆኑ ወላጆች ይሄን ሚናቸውን በአግባቡ መውጣት እንደሚገባቸው አመልክተዋል።

ተማሪዎች የነገ ተረካቢዎች እንደ መሆናቸው መጠን አንድነትና ሕብረት ላይ ማተኮር እንዳለባቸው ነው ዶክተር ቶሎሳ ያስረዱት።

 

 

 

 

    

 

 

 

    

 

 

 

 

 

  

 

 

 

 

 

 

 

  

 

 

 

 

 

 

 

 

 

  

 

 

 

  
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም