በሳይንስ ሙዚየም የተዘጋጀው የግብርና አውደ ርዕይ በዘርፉ ልምድ ለመለዋወጥ እድል ፈጥሯል - የጋምቤላ ክልል እርሻና ተፈጥሮ ኃብት ልማት ቢሮ

144

አዲስ አበባ ግንቦት 25/2015 (ኢዜአ)፦  በሳይንስ ሙዚየም የዘጋጀው የግብርና አውደ ርዕይ በዘርፉ ልምድ ለመለዋወጥ እድል የሚፈጥር መሆኑን የጋምቤላ ክልል እርሻና ተፈጥሮ ኃብት ልማት ቢሮ ገለጸ።

የጋምቤላ ክልል አመራሮችና የፌዴራል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በሳይንስ ሙዚየም የቀረቡ የግብርና ውጤቶችን፣ የዘርፉ ቴክኖሎጂ እንዲሁም በሳይንስ ሙዚየሙ የተዘጋጀውን የጋምቤላ ክልል የግብርና አውደ ርዕይን ተዘዋውረው ተመልክተዋል። 

የጋምቤላ ክልል እርሻና ተፈጥሮ ኃብት ቢሮ ኃላፊ አጃክ ኡቻላ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት ክልሉ የግብርናው ዘርፍ ምርትና ምርታማነት ለመጨመር እየሰራ ነው።  

አውደ ርዕዩ የቀረቡ የፈጠራ ሥራዎችና ቴክኖሎጂዎች ክልሉ ያለውን እምቅ የተፈጥሮ ኃብት በዘመናዊ መንገድ ለመጠቀም የሚያስችል ልምድ ያገኙበት መሆኑን ጠቁመዋል። 

በመሆኑም አውደ ርዕዩ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን ለመጠቀምና የዘርፉን ምርትና ምርታማነት ለማረጋገጥ  መነሳሳት የሚፈጥርና ልምድ የተቀሰመበት መሆኑን ነው የገለጹት።  

ያም ብቻ ሳይሆን በዘርፉ ከተሰማሩ ኩባንያዎች ጋር ትስስር ለመፍጠር እንዲሁም ክልሉ በዘርፉ ያለውን አቅምና ኃብት ለማስተዋወቅም እድል የፈጠረ መሆኑን ጠቁመዋል።
 

በጉብኝቱ ላይ የተገኙት የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ዴኤታ አለሚቱ ኡሞድ በበኩላቸው  ጋምቤላ ከፍተኛ ሃብት ያለው ክልል ነው። 

ይህንንም ዘርፍ በማልማት ለክልሉም ሆኖ ለአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እድገት የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ ጠቁመዋል።  

በመሆኑም በቀጣይ የክልሉን ግብርና በማዘመን ምርታማነት ከማሳደግ ባለፈ የገበያ ትስስር መፍጠር ላይ መንግሥትና ባለሃብቱ ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ ጠይቀዋል።

በተጓዳኝም ወጣቶችና ሴቶችን ከዲጂታል ግብርና ጋር እንዲተዋወቁ መሥራት ያስፈልጋልም ብለዋል።  

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም