የኢትዮጵያ ዳያስፖራዎች በሀገሪቱ የልማት ተሳትፏቸውን ለማሳደግ እየተሰራ ነው- የዳያስፖራ አገልግሎት

190

ባህርዳር ግንቦት 25/2015 (ኢዜአ)፡- በውጭ  የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን የሀገሪቱን  ልማት ለማፋጠን  እያደረጉት  ያለውን ተሳትፎ ለማሳደግ  እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ገለጸ።

አገልግሎቱ ከአማራ ክልል ጋር በመተባበር የዳያስፖራውን ተሳትፎ ለማሳደግ   ያዘጋጀው  የምክክር መድረክ ዛሬ በእንጅባራ ከተማ ተካሄዷል።


 

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ተወካይ አቶ መላኩ ዘለቀ በመድረኩ ላይ፤  የኢትዮጵያ ዳያስፖራ በሀገሩ ሰላምና ልማት ወደ ኋላ እንደማይል ገልጸው፤ ባለፉት ዓመታት ዳያስፖራው በፐብሊክ ዲፕሎማሲ የኢትዮጵያን  ገጽታ በመገንባትና ሀገሪቱ በችግር ውስጥ በነበረችበት ወቅት በ" ኖ ሞር"  እንቅስቃሴ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን አስታውሰዋል።

በተጨማሪም በተፈጠረው ምቹ ሁኔታ በኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ የልማት ዘርፎች በኢንቨስትመንት በመሳተፍ በስራ እድል ፈጠራና ሀገርን በማሳደግ የበኩሉ የድርሻውን እየተወጣ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

ይህም ዕውቀትን፣ ክህሎትንና የቴክኖሎጂ ሽግግርን እንዲሁም አዳዲስ አሰራሮችን ወደ ሀገር በማምጣት ለወጣቱ ትውልድ ለማስተላለፍ ጥረት ማድረጉን ጠቅሰዋል። 

ይህም ሆኖ ካለው የዳያስፖራ ቁጥርና አቅም አንጻር ሲታይ ሀገሪቱ  ከዳያስፖራው የሚገባትን ያህል ጥቅም አግኝታለች ብሎ መናገር እንደማይቻል ተናግረዋል።

በመሆኑም በውጭ  የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን የሀገሪቱን  ልማት ለማፋጠን  እያደረጉት  ያለውን ተሳትፎ ይበልጥ ለማሳደግ  እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ሰላማዊት አለማየሁ፤ በውጭ የሚኖሩ ዳያስፖራዎች የውጭ ምንዛሬ ወደ ሀገር ውስጥ በመላክ፣ ንግድና ቱሪዝሙን በማስፋፋትና የሀገሪቱን  ገጽታ በመገንባት በኩል ዳያስፖራዎች ተጨባጭ ውጤቶች ማስመዝገባቸውን ገልጸዋል።

በቀጣይም እውቀታቸውን ፣ገንዘባቸውንና ልምዳቸውን ተጠቅመው በክልሉ ብሎም በሀገሪቱ ውስጥ መዋዕለ ንዋያቸውን በማፍሰስ    ራሳቸውንና ህዝባቸውን ለመጥቀም በሚያደርጉት እንቅስቃሴ የክልሉ መንግስት ድጋፍ  እንደማይለያቸው አስታውቀዋል።

ለዚህም መሰል የምክክር መድረክ መልካም ጅምሮችን አጠናክሮ ለማስቀጠልና የታዩ ክፍተቶችን ለይቶ ለማስተካከል እንደሚያግዝ ጠቅሰዋል።

በመድረኩ የተሳተፉ የመንግስትና የዳያስፖራ አካላትም በምክክራቸው ለቀጣይ ስራ አቅጣጫ በማስቀመጥ መረባረብ እንደሚጠበቅባቸውም ጠቁመዋል።

በምክክር መድረኩ ከፌዴራል፣ ከክልልና ከሁሉም ዞኖች የተውጣጡ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም