ኮሪያ ሪፐብሊክ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የልማት ትብብር አጠናክራ ትቀጥላለች - አምባሳደር ካንግ ሶኪ

141

አዲስ አበባ ግንቦት 25/2015 (ኢዜአ)፦  ኮሪያ ሪፐብሊክ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የልማት ትብብር አጠናክራ እንደምትቀጥል በኢትዮጵያ የአገሪቱ አምባሳደር ካንግ ሶኪ ገለጹ።  

አምባሳደር ካንግ ለኢዜአ እንደገለጹት ኮሪያ ሪፐብሊክ ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ዲፕሎማሲያዊ በተለይም በልማት መስኮች ያላቸውን ትብብር እየተጠናከረ መምጣቱንና ይህንንም ይበልጥ ለማጠናከር እየተሰራ ነው ብለዋል።   

የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ ኮሪያ ሪፐብሊክ በሰሜን የኢትዮጵያ ክፍል ያላትን የልማት ፕሮጀክቶች መልሶ ለማስጀመር የሚያስችሉ ዝግጅቶች እያደረገች መሆኑን አመልክተዋል።    

የኮሪያ ሪፐብሊክ መንግስት ቀደም ሲል ለኢትዮጵያ 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ዶላር የሰብዓዊ ድጋፍ 10 ሚሊየን ዶላር ግምት ያለው የምግብ ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል።

በቀጣይም ተጨማሪ የሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረግና የተቋረጡ የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶችን ስራ ለማስጀመር እንቅስቃሴ መጀመሩን ነው አምባሳደር ካንግ የጠቀሱት። 

ለሰላም ስምምነቱ ተግባራዊነት የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ ትቀጥላለች ብለዋል።

በቀጣይም የኮሪያ ሪፐብሊክ መንግስት በምስራቅ አፍሪካ ለኢትዮጵያ፣ ኬንያ እና ሶማሊያ ከ20 ሚሊዮን ዶላር በላይ የምግብ እና ሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረግ ማቀዱን ጠቁመዋል። 


 

የኢትዮጵያና ኮሪያ ሪፐብሊክ ወዳጅነት የተጀመረው እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1950ዎቹ ሲሆን ይፋዊ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የተጀመረው እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር 1963 ነው።

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም