የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች የፈጠራ ሥራዎቻቸው ለህዝብ እንዲያስተዋውቁ ድጋፍ ሊደረግላቸው ይገባል -ቱሪዝም ሚኒስቴር

አዲስ አበባ ግንቦት 25/2015 (ኢዜአ)፦የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች የፈጠራ ሥራዎቻቸውን በስፋት ለህዝብ እንዲያስተዋውቁ  ባለድርሻ አካላት ድጋፍ ሊያደርጉላቸው እንደሚገባ ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ስለሺ ግርማ  ተናገሩ።

14ኛው ከተማ አቀፍ የኪነ-ጥበብ ፌስቲቫል በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ ዐውደ ርዕይ እና ሥነ-ጥበባዊ ክዋኔዎች መቅረብ ጀምረዋል።  

የኪነ-ጥበብ መድረኩም "በሥነ- ጥበባት ሕብራዊ መልክ የተዋበች ኢትዮጵያ'' በሚል መሪ  ቃል  ከግንቦት 25 እስከ 27  ይካሄዳል።

ለሶስት ቀናት በሚቆየው በዚሁ ፌስቲቫል በዛሬው ውሎው የተለያዩ የሥነ-ጽሑፍ፣ የኪነ- ጥበብና ሌሎች መሰል ሥራዎች ቀርበውበታል።

ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ስለሺ ግርማ በማስጀመሪያው ወቅት እንዳሉት በኪነ-ጥበብና ሥነ-ጥብብ ዘርፍ የተሰማሩ አካላት የፈጠራ ሥራዎቻቸውን ለሕዝብ እንዲያቀርቡም የኪነ-ጥበብ ፌስቲቫል ፋይዳቸው የጎላ ነው እንደሆነ ገልፀዋል።


 

ኪነ-ጥበብን ወደ ኢኮኖሚ አመንጪነት ለማሳደግ  ፌስቲቫሎችን በጥራት ማዘጋጀት አስፈላጊ ነው ብለዋል ። 

ስለሆነም ከተማ አቀፍ የኪነ-ጥበብ መድረኮች መዘጋጀታቸው በሀገር አቀፍ ደረጃ በመንግሥት የተያዘውን የቱሪዝም ልማት የሚደግፍና ኢኮኖሚያዊ አቅምን የሚያሳድግ ነው ብለዋል።

ይህንንም ለማጠናከር የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች የፈጠራ ሥራዎቻቸውን ለህዝብ እንዲያስተዋውቁ ባለድርሻ አካላት ድጋፍ ሊያደርጉላቸው ይገባል ብለዋል።

የአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ የኪነ-ጥበብ ዘርፍ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ሠርፀ ፍሬስብሐሃት በበኩላቸው መድረኩ በከተማው ያለውን የኪነ-ጥበብ ሀብቶች  አጉልቶ ለማሳየት የሚረዳ  ነው ብለዋል።


 

"ለጥበብ ሥራዎች የክወና መድረክ ከማግኘት በላይ ትልቁ አንቀሳቃሽ ኃይል የሕዝብ እይታና አድናቆት ነው" ያሉት ምክትል ቢሮው ኃላፊ ሥነ-ጥበባዊ ፈጠራዎችንና ፌስቲቫሎችን ማመቻቸት አስፈላጊ የሚሆነውም ለዚህ ነው ብለዋል። 

ከአዲስ አበባ ጋር ተመሳሳይ ተሞክሮዎችን የሚጋሩ የዓለም ከተሞች ዓመቱን ሙሉ በከፍተኛ ጥራት የሚዘጋጁትን የኪነ-ጥበብ ፌስቲቫል ዘርፉን ወደ ኢኮኖሚ አመንጪነት ለመቀየር ከፍተኛ እገዛ እንዳደረገላቸው ገልጸዋል።

የሚመለከታቸው ይህንን እንደ አገር በተሞክሮነት ሊወስዱት ይገባል ያሉ ሲሆን ባለሃብቶች በሚዘጋጁ ፌስቲቫሎች ላይ  በስፋት እንዲሰማሩ  ጥሪ አቅርበዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም