በአማራ ክልል ባለፉት 10 ወራት ከ960 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል ተፈጥሯል-የክልሉ ስራና ስልጠና ቢሮ

113

አዲስ አበባ ግንቦት 25/2015(ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል በተያዘው በጀት ዓመት 10 ወራት ከ960 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል መፍጠሩን የክልሉ ስራና ስልጠና ቢሮ አስታወቀ።

የአማራ ክልል ስራና ስልጠና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አወቀ ዘመነ ለኢዜአ እንደገለጹት በአማራ ክልል አሁን ላይ ያለው የስራ አጥነት ምጣኔ 19 ነጥብ 1 በመቶ ይጠጋል።

በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል የነበረው ጦርነት በክልሉ በሚገኙ ሃብቶች ላይ ያደረሰው መጠነ ሰፊ ውድመት የስራ ፈላጊው ቁጥር እንዲያሸቅብ ማድረጉንም ተናግረዋል፡፡

ይህን ከግምት ውስጥ በማስገባት በተያዘው በጀት ዓመት ለስራ ዕድል ፈጠራ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ ወደ ስራ መግባቱን ገልጸዋል።

በዚህም በ2015 ዓም በጀት ዓመት 1 ሚሊዮን 203 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ሰዎች የስራ ዕድል ለመፍጠር ዕቅድ ተይዞ ወደ ስራ መገባቱን አስታውሰዋል።

ይህን ተከትሎ በበጀት ዓመቱ በተሰራው ስራ ባለፉት 10 ወራት ለ 967 ሺህ 584 ዜጎች የስራ ዕድል መፍጠር መቻሉን ጠቅሰዋል።

አፈጻጸሙ በዓመቱ ከተያዘው እቅድ ውስጥ 80 በመቶውን ያሳካ መሆኑን ነው የገለጹት።

ከዚህ ውስጥ ለ647 ሺህ 520 ዜጎች ቋሚ የስራ ዕድል የተፈጠረላቸው ሲሆን ቀሪዎቹ ጊዜያዊ የስራ ዕድል ያገኙ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በበጀት ዓመቱ በአብዛኛው የተፈጠረው የስራ ዕድል በግብርና፣ በኢንዱስትሪ እና በአገልግሎት ዘርፍ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ክልሉ በበጀት ዓመቱ ለስራ ዕድል ፈጠራ 3 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር መደበኛና ተዘዋዋሪ ብድር ለመስጠት አቅዶ 2 ነጥብ 99 ቢሊዮን ብር ብድር መስጠት መቻሉን ነው የጠቀሱት።

በቀሪዎቹ ሁለት ወራት ተጨማሪ የስራ ዕድል እንደሚፈጠርና አሁን ላይ በክልሉ በስራ ዕድል ፈጠራ በኩል መልካም አፈጻጻም መመዝገቡን ነው የገለጹት።

ባለፈው በጀት ዓመት በክልሉ በአጠቃላይ የተፈጠረው የስራ ዕድል 965 ሺ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

በዚህ ዓመት ቀሪዎቹን ወራቶች ሳይጨምር በ10 ወር ብቻ የተፈጠረው የስራ ዕድል ከቀደመው ዓመት የላቀ መሆኑን በስኬት አንስተዋል።

በቀጣይ ከዚህ በፊት በስራ ዕድል ፈጠራ ዙሪያ ይታይ የነበረውን የተቋማት የቅንጅት ችግር ለመፍታት በርዕሰ መስተዳደሩ የሚመራ የስራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዞች ልማት ምክር ቤት ማቋቋሚያ ደንብ ጸድቆ ወደ ታችኛው መዋቅር እንዲወርድ ተደርጓል ነው ያሉት።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም