ጂንካ ዩኒቨርሲቲ የመጥፋት አደጋ የተጋረጠበትን የ"ኦንጎታ" ቋንቋ ለመታደግ እየሰራሁ ነው አለ

85

ጂንካ ግንቦት 25/2015 (ኢዜአ):-በደቡብ ኦሞ ዞን በና ፀማይ ወረዳ በአምስት የብራይሌ ጎሳ አባላት የሚነገረውን እና የመጥፋት አደጋ የተጋረጠበትን  የ"ኦንጎታ" ቋንቋን ለመታደግ እየሰራ መሆኑን የጂንካ ዩኒቨርስቲ ገለጸ።

በዩኒቨርስቲው የምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ኤሊያስ ዓለሙ ለኢዜአ እንደገለፁት በሀገሪቱ  የመጥፋት አደጋ ከተጋረጠባቸው ቋንቋዎች መካከል በደቡብ ክልል የሚገኘው  "ኦንጎታ አንዱ ነው።


 

አምስት የጎሳ አባላት ባሉት የብራይሌ ብሔረሰብ አባላት የሚነገረው የ"ኦንጎታ" ቋንቋ ከብሔረሰቡ አባላት ሶስቱ ብቻ በትክክል ቋንቋውን እንደሚናገሩም ተናግረዋል።

የቋንቋ ተናጋሪዎቹ እድሜ ከ50 በላይ መሆኑ ደግሞ ቋንቋው የመጥፋት አደጋ እንደተጋረጠበት ማሳያ እንደሆነም ገልጸዋል።

በመሆኑም ጂንካ ዩኒቨርስቲ ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲ ጋር በመተባበር ቋንቋውን  ከመጥፋት አደጋ ለመታደግ ጥረት መጀመሩን አመልክተዋል። 

በዋናነትም በቋንቋው ላይ ያተኮረ የጥናትና ምርምር ስራ እየተካሄደ መሆኑን ገልጸው፤ በተለይ ቋንቋውን ለማስቀጠል  እንዲቻል ከተናጋሪዎቹ ጋር በመተባበር መዝገበ ቃላት ለማዘጋጀት እንቅስቃሴ ተጀምሯል ብለዋል።

ይህም ቋንቋውን ከትውልድ ወደ ትውልድ  እንዲሸጋገር ሚና እንዳለው አውስተዋል።

በእርግጥ የ"ኦንጎታ" ቋንቋ ከየትኛው የቋንቋ ነገድ እንደሚመደብ "እስካሁን አይታወቅም" ያሉት ዶክተር ኤሊያስ፤ ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመቀናጀት  በቋንቋው ላይ የሚሰራው ጥናት ይህንን ለመመለስና  የቋንቋውን ቤተሰብ በሳይንሳዊ መንገድ ለመለየት እንደሚያስችል ተናግረዋል።

በጥናቱ በቋንቋውና በባህሉ ውስጥ ያሉ ጠቃሚ እሴቶችና አገር በቀል ዕውቀቶች ጎልተው እንዲወጡና ተሰንደው ለትውልድ እንዲተላለፉ እንደሚደረግም ገልፀዋል።

በአውሮፓውያን አቆጣጠር ከ1970 እስከ 1990ዎቹ በተሰሩ ጥናቶች የ"ኦንጎታ" ቋንቋ ተናጋሪዎች 89 ሲሆኑ በ2006 በተካሄደው ጥናት ደግሞ ስምንት ብቻ ቀርተዋል።

በአሁኑ ሰዓት አምስት የቋንቋው ተናጋሪዎች ያሉ ሲሆን ከአምስቱ ሶስቱ ብቻ ቋንቋውን በትክክል እንደሚናገሩ አውስተዋል።

የደቡብ ኦሞ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ አቶ ማሞ ካይሲ በበኩላቸው የቋንቋ መዳከምና መጥፋት በአንድ ማህበረሰቡ ውስጥ የሚገኙ ታሪካዊ ፣ ባህላዊና ትውፊታዊ ሀብቶችም አብረው እንዲጠፉ ያደርጋል ብለዋል።

ይህ እንዳያጋጥም መምሪያው  ለመጥፋት የተቃረቡ ቋንቋዎችን ለመታደግ የተለያዩ ተግባራትን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ከተግባራቱ መካከል ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር ቋንቋዎቹ በሥርዓተ ትምህርት ውስጥ የሚካተቱበትን ጥናት የማካሄድ ሥራ እንደሚጠቀስ አመላክተዋል።

መምሪያው አሁን  ላይ  የጂንካ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር  ለ"ኦንጎታ" ቋንቋ ፊደል እያዘጋጀ እንደሚገኝ ገልፀዋል።

በተጨማሪም በባህሉ ውስጥ ያሉ ተረቶች፣ ትውፊቶች፣ ምሳሌያዊ አነጋገሮች እና ባህላዊ መድሐኒት አዘገጃጀት ጥበቦችን የማሰባሰብ እና በመፅሐፍ መልክ እንዲታተሙ የማድረግ ስራ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።


 

ለቋንቋው ፊደል የመቅረፅ ስራው በሂደት ላይ እንደሚገኝ ጠቅሰው ሲጠናቀቅ ቋንቋው በስርዓተ ትምህርት ውስጥ ተካቶ በአፍ መፍቻ ቋንቋነት በአካባቢው ባሉ ትምህርት ቤቶች እንዲሰጥ ይደረጋልም ብለዋል።

የጂንካ ዩኒቨርሲቲ እና የአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ የመጥፋት አደጋ ያጋጠመውን የ"ኦንጎታ" ቋንቋን ለመታደግ ከመምሪያው ጎን በመሆን የጀመሩት የጥናትና ምርምር ስራ ቋንቋውን ለመታደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለውም ገልጸዋል።

መምሪያው ተባባሪ አካላትን በማስተባበር ቋንቋውን ለመታደግ የሚሰሩ ስራዎች ለስኬት እንዲበቁ አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አረጋግጠዋል ።

መምሪያው በዞኑ የሚገኙ የተለያዩ ቋንቋዎች እንዲበለጽጉና የሚጠበቀውን ዕድገት እንዲያሳዩ የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙ ገልጸው ለአብነት የአሪ ቋንቋ ፊደል ተቀርጾለት በትምህርት ስርዓት ውስጥ እንዲካተት መደረጉን አንስተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም