በመዲናዋ በዘንድሮ የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ1 ሚሊየን በላይ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ ነው 

አዲስ አበባ ግንቦት 25/2015(ኢዜአ)፡- በመዲናዋ በዘንድሮ የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መርሃ ግብር ከ1 ሚሊየን በላይ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኅብረተሰብ ተሳትፎና  በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን ገለጸ። 

የኅብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽነር አብርሃም ታደሰ ለኢዜአ እንደገለፁት በመዲናዋ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እየተጠናከረ መጥቷል።    

በዘንድሮ የ2015 የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎትም በመዲናዋ 2 ሚሊየን የሚጠጉ በጎ ፈቃደኞች በተለያዩ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት አይነቶች ይሳተፋሉ ብለዋል።

በጎ ፈቃደኞቹ  በቤት እድሳት፣ በደም ልገሳ፣ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርና በሌሎችም ዘርፈ ብዙ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተሳትፎ እንደሚኖራቸው ገልጸዋል።

ለአብነትም ከ270 በላይ ቤቶች ግንባታና እድሳት ሥራ መጀመሩን ጠቁመው፤ በሌሎች መስኮች በጎ ፈቃደኞቹ ሥራቸውን አጠናክረው መቀጠላቸውንም ተናግረዋል። 

በግንቦት ወር 2015 ዓ.ም ተጀምሮ እስከ ቀጣይ ዓመት መስከረም በሚዘልቀው በዚህ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በመዲናዋ የሚገኙ ከ1 ሚሊየን በላይ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።   

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መርሃ - ግብሩ ውጤታማ እንዲሆን በጎ ፈቃደኞች ባላቸው ጉልበት፣ እውቀትና ገንዘብ ኅብረተሰባቸውን የሚያገለግሉበት ሁኔታዎች መኖራቸውንም አብራርተዋል።

ኮሚሽኑ የሚሰሩ የበጎ ፈቃድ ተግባራት ተጨባጭ ለውጥ እንዲያመጡ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ተሳትፏቸውን እንዲያጎለብቱ ለማድረግ የጀመረውን ሥራ አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

በከተማው ለሚከናወኑ የበጎ ፈቃድ ሥራዎች ከግብ እንዲደርሱ የኅብረተሰቡን የነቃ ተሳትፎ የሚጠይቅ በመሆኑ ነዋሪዎች በሚችሉት አቅም የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበርክቱ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

በዘንድሮም ዓመት በአገር አቀፍ ደረጃ 20 ሚሊየን የሚጠጉ በጎ ፈቃደኞች በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የሚሳተፉ መሆናቸውን የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጹ ይታወሳል።

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም