የጭሮ ከተማ በልዩ የስራ እድል ፈጠራ ፕሮግራም ከ1ሺህ 400 በላይ ወጣቶችን የእድሉ ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የጭሮ ከተማ በልዩ የስራ እድል ፈጠራ ፕሮግራም ከ1ሺህ 400 በላይ ወጣቶችን የእድሉ ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰራ ነው

ጭሮ ግንቦት 25/2015(ኢዜአ):-በጭሮ ከተማ ከ1 ሺህ 400 በላይ ወጣቶችን በልዩ ስራ እድል ፈጠራ ፕሮግራም በጎጆ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ለማሰማራት እየሰራ መሆኑን የከተማው ስራ እድል ፈጠራና ክህሎት ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡
የጭሮ ከተማ ስራ እድል ፈጠራና ክህሎት ጽህፈት ቤት ከባለድርሻ አካላት ጋር መክሯል።
በውይይቱም ለወጣቶቹ ልዩ የስራ ፈጠራ ፕሮግራም እየተመቻቸ መሆኑ ተገልጾ፤ በዚህም በጎጆ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ለ1ሺህ 412 ስራ አጥ የከተማው ወጣቶች የመስሪያ ቦታዎችንና የስራ ማስኬጃ የገንዘብ ብድር ለማመቻቸት ትግበራው መጀመሩ ተገልጿል፡፡
የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ ወይዘሮ ዘሃራ ኢብራሂም በዚሁ ጊዜ እንዳብራሩት የ2015 በጀት ሳይጠናቀቅ በሚተገበረው ስራ ለ1 ሺ 412 የከተማው ስራ አጥ ወጣቶች እድሉን ለማመቻቸት እየሰራ ነው።
ስራው በበላይነት የሚከናወነውም በባድርሻ አካላቱ ትብብር አማካይነት መሆኑን አክለዋል፡፡
ይህን ስራ ተግባራዊ ለማድረግም ወጣቶቹን በ282 ማህበራት በማደራጀት የስራ እድሉ የሚሰራ ሆኖ ለዚህም 7 ሚሊዮን ብር ስራ ማስጀመሪያና 2 ነጥብ 5 ሔክታር መሬት ለመስሪያ ቦታ እንደሚሰጥ ገልፀዋል፡፡
ስራ አጥ ወጣቶቹ እንዲሰማሩበት የተፈለገው የጎጆ ኢንዱስትሪ ዘርፍም የሸክላ ስራ፣ የቆዳ ውጤቶች ስራ፤ ልብስ ስፌትና ሽመና መሆናቸውንም ኃላፊዋ አያይዘው ገልፀዋል፡፡
ሁሉም ባለድርሻ አካላት በሚፈለገው አግባብ ሁሉንም ስራዎች ውጤታማ ለማድረግ የበኩላቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል፡፡
ከውይይቱ ተሳታፊ ባለድርሻ አካላት መካከል የጭሮ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ አመዲን ኢብሮ የከተማችንን ወጣቶች በጎጆ ኢንዱስትሪ ስራዎች ላይ በማሳተፍ የከተማችንን ገጽታ መለወጥ የምንችልበት እድል መፍጠር ነው ብለዋል፡፡
ከተማዋ ባላት አቅም ልክ ወጣቶቹ ስራ ፈጥረው ተጠቃሚ የሚሆኑበትን እድል በማመቻቸት ሰላሟ የተረጋገጠ ከተማን ከመፍጠር ባሻገር ውብና ማራኪ ገፅታን ማላበስ እንደሚቻልም አክለዋል፡፡
የንግድ ስራ ማህበራትን ማሳተፍ ለስራው መፋጠን ትልቅ ጥቅም እንዳለው ጠቁመው በታቀደው ጊዜ ተጠናቆ ለተጠቃሚዎች መድረስ እንዳለበትም ተናግረዋል፡፡
ሌላዋ ተሳታፊ የጭሮ ከተማ ሰራተኛና ማህበራዊ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ፋሲካ እሸቱ የስራ አጥ ቁጥሩን ለመቀነስ የሚደረገውን ጥረት ለማሳካት ችግሩን ከስሩ ከማጥናት መጀመር እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡
ስራ አጥ ወጣቶች ተቀማጭ ገንዘብ የሌላቸው መሆኑን ያገናዘበ የብድር አገልግሎት በመስጠት ለስራው ውጤታማነትና ስኬት ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም አክለዋል፡፡
እንደ ወይዘሮ ፋሲካ ገለጻ በተለይ ባንኮች ለስራ አጦች ልዩ የብድር አገልግሎት በማመቻቸት ቢተባበሩ በገንዘብ እጥረት ምክንያት የሚፈጠረውን ችግር መቅረፍ እንደሚቻል ገልፀዋል፡፡