የሰው ሰራሽ ማዳበሪያ እጥረትን ለማቃለል ያዘጋጀነውን የተፈጥሮ ማዳበሪያ ተጠቅመን ወደዘር ሥራ ገብተናል- የሰሜን ወሎ ዞን አርሶ አደሮች

ወልዲያ ግንቦት 25/2015 (ኢዜአ)፡- የሰው ሰራሽ ማዳበሪያ እጥረትን ለማቃለል በበጋው ያዘጋጁትን 6 ሚሊዮን ኩንታል የሚጠጋ የተፈጥሮ ማዳበሪያ በመጠቀም ቀድመው የሚዘሩ ሰብሎችን እየዘሩ መሆኑን የሰሜን ወሎ ዞን አርሶ አደሮች ገለጹ።

በዞኑ ጉባላፍቶ ወረዳ የአላውሃ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ብርሃን ጎበና ለኢዜኣ እንደገለጹት በበጋ ወቅት 51 ሜትር ኪዩብ የተፈጥሮ ማዳበሪያ አዘጋጅተዋል።

እሳቸውን ጨምሮ የቀበሌያቸው አርሶ አደሮች ሰው ሰራሽ ማዳበሪያ እንዲቀርብላቸው የሚመለከታቸው የአስተዳዳር አካላትን ቢጠይቁም "ይመጣል" ከሚል ውጭ እስካሁን ማዳበሪያ እንዳላገኙ ተናግረዋል።

በእዚህም ቀድሞ ለሚዘራው ማሽላ ሰው ሰራሽ ማዳበሪያው እንዳልደረሰላቸው ገልጸው፣ በእዚህም በበጋው ያዘጋጁትን የተፈጥሮ ማዳበሪያ በማሳቸው ላይ ቀድመው በመበተን ማዋሀዳቸውን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅትም ማሽላ ለመዝራት መቻላቸውን ነው የገለጹት።

"ሰው ሰራሽ ማዳበሪያው ቀድሞ ለተዘራው ማሽላ ባይደርስም በመጪው ሰኔ ወር ለሚከናወነው የዘር ሥራ የሚመለከተው አካል ፈጣን መፍትሄ ይስጠን" ሲሉ ጠይቀዋል።

በራያና ቆቦ ወረዳ የወርቄ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ከተማ አበጋዝ በጓሯቸው በበጋው ወቅት ያዘጋጁትን 51 ሜትር ኪዩብ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ማሳቸው ላይ ላይ በመበተንና በማዋሃድ ማሽላ መዝራታቸውንም ተናግረዋል።

ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ የህልውና ጉዳይ በመሆኑ ከመጪው ሰኔ ወር አጋማሽ ጀምሮ ለሚዘሩት ጤፍ፣ ስንዴና ሌሎች ሰብሎች ዘር ፈጥኖ እንዲቀርብላቸው ጠይቀዋል።

ከሰብልና ከእንስሳት ተረፈ ምርትና ከአካባቢ ግብአት የተፈጥሮ ማዳበሪያ ማዘጋጀታቸውን የገለጹት አቶ ከተማ፣ "ይህም ለማዳበሪያ የሚያወጡትን ወጭ ከማስቀረት ባለፈ የማዳበሪያ እጥረት ችግሩን ለመሻገር ያስችላል" ብለዋል።

በሰሜን ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ የግብዓት አቅርቦት ቡድን መሪ አቶ ፀጋ ውቤ በበኩላቸው፣ ለ2015/16 የመኽር እርሻ ከሚያስፈልገን 153ሺህ ኩንታል ሰው ሰራሽ ማዳበሪያ እስካሁን ወደዞኑ የገባው 24ሺህ ኩንታል ብቻ ነው።

"ቀሪው ማዳበሪያ ወደብ ላይ መድረሱንና በመጓጓዝ ላይ ስለመሆኑ በሚመለከተው አካል ተገልጾልናል" ያሉት አቶ ጸጋ፣ ማዳበሪያው እንደደረሰ በፍትሀዊነት ለአርሶ አደሩ እንደሚሰራጭ አመልክተዋል።

አርሶ አደሮቹን በመደገፍ ከ5 ነጥብ 9 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ በላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ በማዘጋጀት 3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ የሚሆነውን ቀደሞ ለሚዘሩ ሰብሎች ጥቅም ላይ መዋሉን ገልጸዋል።

በተጨማሪም 23ሺህ 320 ሜትር ኪዩብ የባዮ ጋዝ ሰለሪ፣ ከ9ሺህ ኩንታል በላይ የቨርሚን ኮምፖስት ተዘጋጅቶ ጥቅም ላይ የዋለ ሲሆን፣ ይሄም ለአፈር ለምነትና ለምርታማነት ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን አስረድተዋል።

ጥራጥሬና ጤፍ የሚዘራበት የክረምት ወቅት ሳያልፍ ለዞኑ የሚያስፈለገውን ሰው ሰራሽ ማደበሪያ ለማቅረብ ከሚመለከታቸው ጋር በመነጋገር ላይ መሆናቸውንም አቶ ጸጋ አስታውቀዋል።

በሰሜን ወሎ ዞን ለ2015/16 የምርት ዘመን 231ሺህ 578 ሄክታር መሬት በዘር በመሸፈን ከ6 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ ከዞኑ ግብርና መምሪያ የተገኘ መረጃ ያመላክታል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም