በምዕራብ ወለጋ ዞን የሩዝ ምርትን በዞኑ ምቹ ስነ ምህዳር ባላቸው ወረዳዎች ለማስፋት እየተሰራ ነው - የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት

123

ጊምቢ ግንቦት 25/2015 (ኢዜአ):- በምዕራብ ወለጋ ዞን በሙከራ ደረጃ የነበረውን የሩዝ ምርት በዞኑ ምቹ ስነ ምህዳር ባላቸው ወረዳዎች ለማስፋት እየተሰራ መሆኑን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት አስታወቀ። 

በዞኑ ከ112 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች በሩዝ ምርቱ ላይ እየተሳተፉ እንደሚገኝ ገልጿል። 

ከዚህ ቀደም በምዕራብ ወለጋ ዞን የነበሩ አርሶ አደሮች ኑሮ በቡና ምርት ላይ ብቻ የተወሰነ ነበር። 

ይሁንና የሩዝ ምርት በማይታወቅበት ዞን ላለፈው ሁለት ዓመት በገንጂ ወረዳ የሩዝ ምርት በሙከራ (ፓይለት) ደረጃ ሲመረት ቆይቷል። 

የዞኑ የግብርና ጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ፈይሳ ሀምቢሳ እንደገለጹት በግብርና ባለሙያዎች እገዛ የሩዝ ምርት እየተለመደ መምጣቱን እና ምርቱ በክልሉ መንግስት ትኩረት ከተሰጣቸው ኢንሼቲቮች መካከል እንደሚገኝበት ገልጸዋል።

በዚህም በዞኑ ለሩዝ ምርት አመቺ  በሆኑ ወረዳዎች ምርቱን ለማስፋት እየተሰራ እንደሚገኝ አመልክተዋል።


 

በዘንድሮ ዓመት 88 ሺህ 127 ሔክታር መሬት በላይ በሩዝ ምርት በመሸፈን ከ3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የሩዝ ምርት ለማምረት መታቀዱን ጠቁመዋል። 

እስካሁን በተከናወነው ስራ  ከ2 ሺህ 205 ሔክታር መሬት በላይ በዘር ለመሸፈን መቻሉን ነው አቶ ፈይሳ የተናገሩት።

ለዚህም የሚያስፈልጋቸው የአፈር ማዳበሪያ ከ100 ሺህ ኩንታል በላይ ለአርሶ አደሩ ቀርቦ እንደሚሰራጭ ገልጸዋል።

በምዕራብ ወለጋ ዞን ከ112 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች በሩዝ ምርቱ ላይ እየተሳተፉ መሆናቸውን አመልክተዋል።

የኦሮሚያ ክልል መንግስት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአርሶ አደሩን ኑሮ ለማሻሻል እንዲሁም ምርትና ምርታማነት ለመጨመር የተለያዩ የግብርና ኢንሺቲቮችን ቀርጾ በስራ ላይ ማዋሉን ተናግረዋል። 

በግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች የአርሶ አደሮችን አመለካከት በመቀየር ሩዝ በዓመት ሁለትና ከዚያ በላይ በማምረት ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በተጨማሪም የበጋ መስኖና ሌሎች ገበያ ተኮር ሰብሎች እንዲያመርቱ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

በሩዝ ምርቱ ላይ ተሳታፊ የሆኑ አርሶ አደሮች በበኩላቸው ከሁለት ዓመት በፊት በበጋ መስኖ ስንዴ በማምረት ተጠቃሚ መሆናቸውን አስታውሰው አሁን ላይ በሩዝ ምርት ላይ ከሌሎች አርሶ አደሮች ጋር በባለሙያ እገዛ እያመረቱ መሆኑን ገልጸዋል።

የባለሙያን ምክር በአግባቡ በመጠቀም የተሻለ ምርት ለማግኘት በትኩረት እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም