ጥራትና ደረጃውን የጠበቀ የምግብ አመራረት ስርዓት እውን እንዲሆን የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች ሙያዊ እገዛ ተጠየቀ

163

አዳማ ግንቦት 25/2015  (ኢዜአ) ደህንነቱ የተረጋገጠና ጥራትና ደረጃውን የጠበቀ የምግብ አመራረት ስርዓት እውን ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች በሙያቸው ማገዝ እንደሚገባቸው የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት አስገነዘበ።

ከፌዴራልና ክልሎች የተውጣጡ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች የተሳተፉበትና ጥራት ያለው የምግብ ደህንነት ማረጋገጥ በሚቻልበት ሂደት ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ በአዳማ በመካሄድ ላይ ይገኛል።


 

የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ቦንሳ ባይሳ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት የምግብ ደህንነት ማረጋገጥ የሚቻለው ከምርት ሂደት ጀምሮ እስከ አመጋገብ ድረስ ያሉትን ሂደቶች ጥራት መጠበቅ ሲቻል ነው።

"ለምግብ ደህንነት መረጋገጥ ቅንጅታዊ አሰራርን ማጠናከር ይገባናል" ያሉት አቶ ቦንሳ፤ በዚህም ከሚዲያ አካላት ጋር በትብብር ለመስራት የሚያስችል አቅም ለመፍጠር ያለመ መድረክ ተዘጋጅቷል ብለዋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ5ኛ ጊዜ በሀገራችን ለ4ኛ ጊዜ የሚከበረውን የምግብ ደህንነት ቀን ምክንያት በማድረግ የምግብ ደህንነት ሳምንት እየተከበረ መሆኑንም ተናግረዋል።

በዚህም የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች ከእርሻ ስራው ጀምረው እስከ አመጋገብ ድረስ ጥራትና ደረጃውን የጠበቀ ምግብ እንዲመረት የሚደረገውን ቁጥጥር፣ ክትትልና ድጋፍ ማገዝ እንደሚገባቸው ምክትል ዳይሬክተሩ አስገንዝበዋል።

በተለይም ምግቦች ከሚመረቱበት ግብዓትና ፋብሪካዎች ጀምሮ ያለውን የምግብ ደህንነት፣ ቁጥጥርና ክትትሉ  ውጤታማ እንዲሆን በባለቤትነትና ከኢንስቲትዩቱ ጋር ሆነው በሙያቸው እንዲያግዙ ለማስቻል ጭምር መድረኩ አስፈልጓል ብለዋል።

አክለውም የሀገሪቱን የምግብ ምርቶች ጥራትና ደረጃቸውን ለማስጠበቅ የተዘረጉ አሰራሮች፣ የሕግ ማዕቀፎችና ፖሊሲዎች ውጤታማ እንዲሆኑና የተፈለገው ውጤት እንዲመዘገብ ከሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፍ ብዙ ይጠበቃል ብለዋል።

በኢትዮጵያ የምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን የምግብ ደህንነት ምዝገባና ፍቃድ ዳይሬክተር አቶ በትረ ጌታሁን በበኩላቸው ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡና የሚወጡ የምግብ ምርቶችን ጥራትና ደህንነት ለማስጠበቅ በሚደረገው እንቅስቃሴ ውስጥ የሚዲያ አካላት የጎላ ተሳትፎ ሊኖራቸው ይገባል ብለዋል።

በዚህም በተለይ የምግብ ምርቶች ጥራትና ደረጃቸውን በማስጠበቅ ላይ በትብብር መስራት አለብን ብለዋል።

ዜጎች ደህንነቱ የተጠበቀና ለሰውነት ግንባታ የሚውል የተመጣጠነ ምግብ  እንዲያገኙ ለማስቻል የሚደረገውን ጥረት የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች ሊያግዙን ይገባል ነው ያሉት።

በመድረኩ የምግብ ደህንነት ማረጋገጥ በሚቻልበት ሂደት ላይ መነሻ የውይይት ጽሁፎችና አሰራሮች ቀርበው ይመክርባቸዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም