በሐረሪ ክልል ማህበረሰቡን በማስተባበር ሰላምና ፀጥታን የማስከበሩ ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ፖሊስ አስታወቀ

ሐረር  ግንቦት 25 / 2015 (ኢዜአ) ፡- በሐረሪ ክልል   ማህበረሰቡን በማስተባበር ፅንፈኝነትን በመከላከል  ሰላምና ፀጥታን  የማስከበሩ ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን የክልሉ  ፖሊስ  ኮሚሽን አስታወቀ። 

የክልሉ ፖሊስ  ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ገናነው ጥበበ ለኢዜአ እንዳመለከቱት፤ የክልሉ ማህበረሰብ አንድነቱን በመጠበቅ  በሰላም ጉዳይ ላይ ያገባኛል በሚል በፀጥታ ጥበቃና ህግ ማስከበር ላይ እኩል ተሳትፎ እያደረገ ይገኛል፡፡

ባለፉት ዘጠኝ  ወራት በተደረገው እንቅስቃሴ  በክልሉ የወንጀል ተግባር  12 በመቶ መቀነስ መቻሉን ተናግረዋል፡፡

የወንጀል ድርጊት ሊቀንስ የቻለውም የክልሉ ህዝብ የሰላሙ ባለቤት በመሆን በማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አደረጃጀቶች ውስጥ በመሳተፍ በየዕለቱ እያከናወናቸው በሚገኘው የቁጥጥርና ፍተሻ ተግባር መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የሰላምን ስራ በፖሊስ አካላት ብቻ ማረጋገጥ የማይቻል ነው ያሉት  ምክትል ኮሚሽነሩ፤ ማህበረሰቡ የፖሊስ አጋር በመሆን  የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

በክልሉ የፅንፈኝነት አመለካከትን ቀድሞ ለመከላከልም ተሰሚነት ካላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በቅርበት በመወያየት እየተሰራ መሆኑን  ተናግረዋል፡፡

በክልሉ የተጀመረውን የፅንፈኝነትና ፀረ ሰላም እንቅስቃሴን ቀድሞ የመከላከል ስራም ማህበረሰቡን ባሳተፈ መልኩ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ምክትል ኮሚሽነር ገናነው ገልጸዋል፡፡

በሐረሪ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አገልግሎት  ዳይሬክተር ምክትል ኮማንደር ታጁ ኡመር፤ ማህበረሰቡ ከፖሊስ ጋር ተቀናጅቶ መስራቱ በሰላም እሴት ግንባታው ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ተናግረዋል፡፡


 

በተለይ ማህበረሰቡ በሰላም አደረጃጀቶች መሳተፉ እርስ በእርስ እንዲተዋወቅና ሰላሙን በጋራ እንዲጠብቅ በማስቻሉ በየአካባቢው ይከሰቱ የነበሩ   ወንጀሎች መቀነሱን አመልክተዋል፡፡

ወንጀልን ቀድሞ በመከላከል ብሎም ተፈፅሞ ሲገኝ የህግ ተጠያቂነት እንዲኖር ለማድረግ ዘርፈ ብዙ ተግባራት መከናወናቸውን  የገለጹት የክልሉ  ፖሊስ ኮሚሽን ገለልተኛ አማካሪ ምክር ቤት ስራ አስፈፃሚ አባል አቶ ሲሳይ በቀለ ናቸው።  

ሐረር የምታወቀው በሰላምና በአብሮነት ብሎም በመቻቻል ነው ያሉት አቶ ሲሳይ ፤ ማህበረሰቡ በሰላም ስራው ላይ መሳተፉ አብሮነቱን ይበልጥ እያጎላው መምጣቱን ተናግረዋል፡፡

በክልሉ የአባድር ወረዳ ነዋሪ  አቶ ቡሽራ ያሲን በሰጡት አስተያየት፤ ሰላም ለእያንዳንዱ ማህበረሰብ አስፈላጊ በመሆኑ በፈረቃ በመውጣት የአካባቢያቸውን ሰላም በመጠበቅ ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡


 

 በተለይ ሰላምን በፖሊስ ብቻ ማረጋገጥ ስለማይቻል  ከፖሊስ ጎን በመሆን ፍተሻ በማካሄድና አጠራጣሪ ሁኔታ ሲያግጥም  ጥቆማ በመስጠት  በሰላም ግንባታው ላይ ሃላፊነታቸውን እየተወጡ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

የሸንኮር ወረዳ ነዋሪ  ወጣት ሰለሞን ፍቃዱ ፤ ተሸከርካሪዎች ሥርዓት  ጠብቀው እንዲያሽከረክሩ ከማድረግ ባሻገር የባጃጅ ላይ ስርቆትን በመከላከል ላይ እንደሚገኙ  ገልጿል፡፡


 

በተጨማሪም  የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴዎችና ሌሎች ወንጀሎችን መከላከል በኮሚኒቲ ፖሊሲንግ አደረጃጀት በትብብር እየሰሩ መሆናቸውን ጠቅሶ፤  የኮንትሮባንድ ቁሶችን በቁጥጥር ስር አውለው ለህግ ማቅረባቸውን ጠቁሟል፡፡

የማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አገልግሎት ስራ በክልሉ  በከተማና በገጠር   በየዕለቱ ተጠናክሮ መቀጠሉን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን አመልክቷል፡፡

 

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም