በኦሮሚያ ክልል በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ከ120 በላይ ኢንዱስትሪዎች ዳግም ወደ ስራ ገብተዋል - የክልሉ ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ቢሮ - ኢዜአ አማርኛ
በኦሮሚያ ክልል በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ከ120 በላይ ኢንዱስትሪዎች ዳግም ወደ ስራ ገብተዋል - የክልሉ ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ቢሮ

አዲስ አበባ ግንቦት 25/2015(ኢዜአ)፡- በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ ምክንያቶች ስራ አቁመው የነበሩ ከ120 በላይ ኢንዱስትሪዎች በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ዳግም ወደ ስራ መግባታቸውን የኦሮሚያ ክልል ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ቢሮ ገለጸ፡፡
እንደ አገር የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ከተጀመረ አንድ ዓመት ወዲህ በርካታ ኢንዱስትሪዎች ወደ ስራ መግባታቸው የሚታወቅ ሲሆን ሌሎች ስራ አቁመው የነበሩ ኢንዱስትሪዎችም ዳግም ወደ ስራ ተመልሰዋል፡፡
በንቅናቄው ለኢንዱስትሪዎችና ኢንተርፕራይዞች የተቀናጀ የአቅም ግንባታ፣ የፋይናንስና የግብዓት አቅርቦት ድጋፍ ተድርጎ የማምረት አቅማቸው ከፍ እያለ መምጣቱም ይታወቃል፡፡
በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በተለይ በጨርቃ ጨርቅ፣ በምግብና ምግብ ነክ፣ በማኑፋክቸሪንግና ኢንዱስትሪ ምርቶች ዘርፈ ብዙ ውጤቶች መመዝገባቸውንም እንዲሁ፡፡
የኦሮሚያ ክልል ኢንቨስትመንት እና ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ አቶ አህመድ እድሪስ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ ንቅናቄው በክልሉ ለሚገኙ ኢንዱስትሪዎች መነቃቃት ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡
ንቅናቄው ተግባራዊ ከተደረገ ወዲህ ኢንዱስትሪዎች ከፍተኛ ምርት እንዳያመርቱ ማነቆ የሆኑባቸው ችግሮች ተለይተው መፈታታቸውን ጠቁመዋል፡፡
በክልሉ ስራ አቁመው የነበሩ ከ120 በላይ ኢንዱስትሪዎች የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ከተጀመረ ወዲህ ዳግም ወደ ስራ መግባታቸውን ተናግረዋል፡፡
ስራ የገቡት ኢንዱስትሪዎችም ከፍተኛ፣ መካከለኛ እና አነስተኛ የሚባሉ ስለመሆናቸውም በመጠቆም፡፡
በተጨማሪም በቅንጅት በተሰራው ስራ ከ2 ሺ በላይ ፕሮጀክቶች ወደ ግንባታ እንዲገቡ መደረጉንም ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በክልሉ የሚገኙ ኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም ከፍ ማድረጉን ጠቁመው፤ 41 በመቶ የነበረውን አማካኝ የማምረት አቅም ወደ 51 ከፍ ማድረጉን ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በአገር አቀፍ ደረጃ ሚያዚያ 29 ቀን 2014 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ይፋ መደረጉ ይታወቃል።