በሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ከ76 በመቶ በላይ የሚሆነውን ቦታ ከልቅ ግጦሽ ነጻ ማድረግ ተችሏል - የፓርኩ ጽህፈት ቤት

223

ጎንደር ግንቦት 25/2015 (ኢዜአ):- በሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ከ76 በመቶ በላይ የሚሆነውን የፓርኩን ቦታ ከልቅ ግጦሽና ከእንስሳት ንክኪ ነጻ ማድረግ መቻሉን የፓርኩ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

በአውሮፓውያኑ የዘመን ቀመር በ1978 በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት  (ዩኔስኮ) በዓለም የተፈጥሮ ቅርስነት የተመዘገበው ፓርኩ 412 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ስፋት አለው።


 

ማራኪና ድንቅ የተፈጥሮ አቀማመጥ ያለው ብሔራዊ ፓርኩ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙትን ዋልያ፣ ቀይ ቀበሮና ጭላዳ ዝንጀሮን ጨምሮ የብርቅዬ እጽዋት፣ የዱር እንስሳትና አዕዋፋት መገኛ ስፍራም ነው። 

የውጭና የአገር ውስጥ ጎብኚዎችን በመሳብ የቱሪዝም ገቢ እያስገኘ ነው።

ይሁን እንጂ በፓርኩ ዙሪያ የሚኖሩ ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ በመጨመሩ ለእርሻ፣ ለልቅ ግጦሽና ለቤት መስሪያ በሚል ወደ ፓርኩ በመግባታቸው ብርቅዬ እንስሳት ከፓርኩ ለመራቅ መገደዳቸውን የፓርኩ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አዛናው ታረቀኝ ለኢዜአ ገልጸዋል።

በተጨማሪም የፓርኩ አዋሳኝ ከሆኑት አምስት ወረዳዎች ከዚህ ቀደም በሺዎች የሚቆጠሩ የተለያዩ የቤት እንስሳት የግጦሽ ሳር ፍለጋ ወደ ፓርኩ በመግባት ጉዳት ያደርሱ እንደነበር አስታውሰዋል። 

ፓርኩ የተጋረጡበትን ችግሮች ለመፍታት ባለፉት 10 ዓመታት የልቅ ግጦሽ ቅነሳ ስትራቴጂ ተግባራዊ ማድረጉንና በዚህም ከ76 በመቶ በላይ የሚሆነውን የፓርኩን ክልል ከልቅ ግጦሽና የቤት እንስሳት ንክኪ ነጻ መደረጉን አመልክተዋል።

በስትራቴጂው ግብረ ኃይል ከማቋቋም ባለፈ ሕብረተሰቡ እንስሳቱን በቤት ውስጥ አስሮ ቢቀልብ የስጋና የወተት ምርታማነትን በማሳደግ የተሻለ ተጠቃሚ እንደሚሆን ግንዛቤ በመፈጠሩ ፓርኩን ከንክኪ ነጻ ለማድረግ መቻሉን ነው አቶ አዛናው ያስረዱት።

አብዛኛው የፓርኩ ክልል ነጻ መደረጉ በውስጡ የሚገኙ ዋልያ፣ ጭላዳ ዝንጀሮዎችና ድኩላዎች ዓመቱን ሙሉ የእጽዋትና የሳር መኖዎችን እንዲያገኙና እንዲባዙ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ገልጸዋል።

ከቤት እንስሳቱ ጋር ወደ ፓርኩ ክልል በሚገቡ ውሾች አማካኝነት በቀይ ቀበሮዎች ላይ ይደርስ የነበረውን የእብድ ውሻ በሽታ ስርጭትን በመቆጣጠር የመጥፋት ስጋታቸውን ለመቀነስ እንደተቻለ ተናግረዋል።

"በተጨማሪም የዱር እንስሳቱ መኖና ውሃ ፍለጋ ብዙ ኪሎ ሜትሮችን ሲጓዙ ይደርስባቸው የነበረው እንግልት ቀርቷል" ነው ያሉት የፓርኩ ጽህፈት ቤት ኃላፊ።

በአሁኑ ወቅት የዱር እንስሳቱ ከቦታ ቦታ በነጻነት ለመንቀሳቀስ የሚያስችላቸው ምቹ ሁኔታ መፈጠሩንና የመራቢያና የመኖሪያ ቦታዎቻቸውንም ከተለያዩ አደጋዎች መጠበቅ መቻሉን ጠቁመዋል።

በቀጣይ ፓርኩን ሙሉ በሙሉ ከንክኪ ነጻ ለማድረግም አምባራስ እና አበርጊና በሚባሉ አካባቢዎች  ያሉ ነዋሪዎችን ወደ ሌላ አካባቢ ማስፈር እንደሚያስፈልግ የገለጹት አቶ አዛናው ለዚህም መንግስትና የሚመለከታቸው አካላት የበኩላቸውን እገዛ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

የደባርቅ ከተማ የኢኮ ቱሪዝም ዩኒየን ሊቀመንበር አቶ ሞገስ አየነው በበኩላቸው የቱሪስቶችን እቃዎች የሚያጓጉዙ የዩኒየኑ አባላት ፈረሶችና በቅሎዎች በፓርኩ ውስጥ እንዳይሰማሩ ስምምነት ላይ ተደርሶ መተግበሩን ገልጸዋል።

በፓርኩ ለጎብኚዎች አገልግሎት በመስጠት ገቢ እያገኙ ያሉት ከ8 ሺህ በላይ የዩኒየኑ አባላት የፓርኩን ብዝሃ ሕይወት በመጠበቅ እና በመንከባከብ የድርሻቸውን እየተወጡ መሆኑን አመልክተዋል።

በደባርቅ ወረዳ የሚሊገብሳ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ሙሉቀን ግስሙ የቀበሌው ነዋሪ ለዱር እንስሳቱ ሕልውና ቅድሚያ በመስጠት የግጦሽ ሳር ፍለጋ የቤት እንስሳቶቻችንን ወደ ፓርኩ ክልል ከማሰማራት መቆጠቡን ገልጸዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም