በሀገር አቀፍ ደረጃ አንድ ወጥ የግብርና መረጃ ቋት እየተዘጋጀ ነው - የግብርና ሚኒስቴር

105

አዳማ ኢዜአ ግንቦት 25/2015(ኢዜአ):- የግብርና ሚኒስቴር በአገር አቀፍ ደረጃ አንድ ወጥ የሆነ ዘመናዊ የግብርና መረጃ ስርዓት ለመዘርጋት የሚያስችል የመረጃ ቋት እየተዘጋጀ እንደሚገኝ አስታወቀ።

የግብርና መረጃ የባለድርሻ አካላት አውደ ጥናት በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ነው።

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ፍቅሩ ረጋሳ እንደገለጹት በግብርናው ላይ ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት እየተከናወኑ ያሉ ስራዎችን ጥራት ባለው ወቅታዊ መረጃ መደገፍ ይገባል።

በሚኒስቴሩ በእንስሳት እና ዓሳ ዘርፍ ብቻ ስምንት የመረጃ ቋት መኖራቸውንና በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ዘርፎች ተበታትነው ያሉትን ወደ አንድ በማምጣት ዲጂታል የሆነ አገራዊ የመረጃ ቋት የማዘጋጀት ስራ እየተከናወነ ነው ብለዋል።


 

አገራዊ የሆነ አንድ የመረጃ ቋት መገንባት የመረጃ ድግግሞሽና የመረጃ ጥራት በማስጠበቅ ኢትዮጵያ የዲጂታል የመረጃ ስርዓት ማዕከል እንዲኖራት የሚያስችል እንዲሁም ወጪ ቆጣቢ በመሆን የእውቀት፣ የጉልበት እና ሀብት ብክነትን የሚያስቀር መሆኑን አመልክተዋል።

የሚገነባው አገራዊ የመረጃ ቋት በቅንጅት መረጃ ለመሰብሰብ፣ ለማጋራት እና ለመጠቀም እንደሚያስችልም ተናግረዋል።

የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢኒስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ማንደፍሮ ንጉሴ በበኩላቸው መረጃ አሁን ያለውን የግብርና ስርዓት ለመለወጥ እና ለማዘመን ዲጂታል የሆነ የመረጃ አሰባሰብና አጠቃቀም ወሳኝ ነው ብለዋል።


 

ባለድርሻ አካላት አንድ አገራዊ የመረጃ ቋት እንዲገነባ የበኩላቸውን ድጋፍ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው አመልክተዋል።

በአውደ ጥናቱ ላይ የግብርና ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢኒስቲትዩት፣ የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ እና ጂኦ-ስፓሻል ኢንስቲትዩት፣ የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት እና የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት በመረጃ አሰባሰብና ዲጂታላይዜሽን በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል።

የግብርና መረጃን የባለድርሻ አካላት አውደ ጥናት እስከ ነገ ይቆያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም