የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ድርቅ በአርብቶ አደሩ ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ገለጸ

334

ቡሌ ሆራ ግንቦት 25/2015 (ኢዜአ):- የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ድርቅ በአርብቶ አደሩ ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ አስታወቀ።


የተፈጥሮ ሃብት አጠባበቅ ስራዎችን ከማጠናከር ባለፈ አማራጭ የውሃ አጠቃቀም ስርዓት በመዘርጋት ችግሩን ለመቅረፍ መሰራት እንደሚገባም ተገልጿል።

የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ”አርብቶ አደርና የአየር ንብረት ለውጥ ተጽኖ” በሚል መሪ ቃል ያዘጋጀው ሶስተኛውን ዓለም አቀፍ የጥናት እና ምርምር አውደ ጥናት እያካሄደ ነው።


 


የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ፍቃዱ ወልደማርያም እንዳሉት ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማር ስራው ጎን ለጎን በግብርና፣ በጤና፣ማዕድን እና አገር በቀል እውቀቶች የልህቀት ማዕከል ለመሆን እየሰራ ነው ብለዋል ።


በተለይም በጉጂ እና ቦረና ዞኖች የአየር ንብረት ለውጥ በግብርና ልማቱ እና በእንሰሳት እርባታ እያደረሰ የሚገኘውን ጉዳት ለመቀነስ ዘርፍ ብዙ ጥረቶች እየተደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።


በተለይ ምርምርን መሰረት ያደረገ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ እንዲጠናከር እንዲሁም በቆላማ አካባቢዎች የሚገኘውን ዝቅተኛ የውሃ መጠን በአግባቡ ለመጠቀም በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል ።


አውደ ጥናቱ በዘርፉ ዓለም አቀፍ የእውቀትና የልምድ ልውውጥ በማድረግ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖ ለመቀነስ የሚደረገውን ጥረት ያግዛል ነው ያሉት ዶክተር ፍቃዱ።


 


የአፍሪካ የአከባቢ ጤና ማህበር ፕሬዝዳንት ዶክተር ተዋበች ቢሻው በበኩላቸው በአየር ንብረት ለውጥ ችግር የሚፈጠረውን የውሃ እጥረት ከእርባታ ስርዓቱ እና የገበያ ትስስር ውስንነት ጋር ተዳምሮ በኢትዮጵያ የእንስሳት ሀብት ላይ ጫና እያሳደረ ነው ብለዋል።


የተፈጥሮ ሀብት አጠባበቅ ስራዎችን ከማጠናከር ባለፈ አማራጭ የውሃ አጠቃቀም ስርዓት በመዘርጋት ችግሩን ለመቅረፍ መስራት እንደሚገባ አመልክተዋል።


በዚህ ረገድ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጥናት እና ምርምር ከማድረግ ባለፈ የጥናት ውጤትን መሰረት ያደረገ ትግበራ በማከናወን የበኩላቸውን ኃላፊነት መወጣት እንዳለባቸው ተናግረዋል።


በአውደ ጥናቱ ላይ ምሁራን፣የአገር ውስጥ እና የውጭ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እንዲሁም የመንግስት እና የግል ድርጅቶች ተሳታፊ መሆናቸው ተገልጿል።


እስከ ነገ በሚቆየው አውደ ጥናት ከ40 በላይ የጥናት ውጤቶች ይቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም