በጋምቤላ ክልል የሕጻናት የመቀንጨር ችግርን ለመከላከል በተደረገው ጥረት መሻሻል ታይቶበታል- የክልሉ ጤና ቢሮ

166

ጋምቤላ ግንቦት 25/2015( ኢዜአ)፡- በጋምቤላ ክልል በተመጣጠነ ምግብ እጥረት የሚያጋጥመውን የሕጻናት መቀንጨር ችግር  ለመከላከል በተደረገው ጥረት መሻሻል መታየቱን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ።

በቢሮው የእናቶች እና ሕጻናት ጤና አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ ኡጁሉ ኡሞድ ፤ በክልሉ በተመጣጠነ ምግብ እጥረት የሚቀነጭሩ ሕጻናትን ለመቀነስ በተደረገው ጥረት የመጠነ መቀንጨር ምጣኔን እ.አ.አ  በ2000 37 በመቶ የነበረውን ወደ 17 በመቶ ዝቅ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።

ይህም ከአገር አቀፍ የመጠነ መቀንጨር ምጣኔ ጋር ሲነጻጸር ከግማሽ በላይ በመቀነስ መሻሻል መታየቱን አመልክተዋል።

የሚቀነጭሩ ሕጻናት ቁጥር በመቀነስ ረገድ የተገኘው ውጤት በዘርፉ የተጠናከረ ግንዛቤ የመፍጠር ስራ በመከናወኑ እንዲሁም በአካባቢው ማህበረሰብ ጥሩ የአመጋገብ ዘይቤ እና ምቹ የተፈጥሮ ሀብት በመኖሩ ነው ብለዋል።

በሌላ በኩል በምግብ እጥረት ምክንያት የሚቀጭጩ ሕጻናት ቁጥር ከፍተኛ መሆኑንና የሚቀጭጩ ሕጻናት ቁጥር 12 ነጥብ 6 በመቶ መሆኑን ጠቁመዋል።

ይህም ከአገር አቀፉ በ5 ነጥብ 6 በመቶ ብልጫ እንዳለው ነው ዳይሬክተሩ ያመለከቱት።  

በአንጻሩ በክልሉ በምግብ እጥረት የሚቀጭጩ ሕጻናት ቁጥር ከፍተኛ ሊሆን የቻለው በየዓመቱ በወንዞች ሙላት ምክንያት በሚከሰት የጎርፍ አደጋ መፈናቀልና ሌሎች ምክንያቶች እንደሆነ ጠቅሰው ችግሩን ለማቃለል እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

የጤና ቢሮው እንደ አገር እ.አ.አ በ2025 በተመጣጠነ ምግብ እጥረት የሚታየውን የሕጻናት መቀንጨር ችግር ለመቀነስ የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት በሌማት ትሩፋት መርሐ-ግብር በመታገዝ እቅዱን ለማሳካት እየሰራ ነው ብለዋል።


 

የጋምቤላ ክልል የኢታንግ ልዩ ወረዳ የስርዓተ ምግብ አስተባባሪ አቶ ማሞ አበበ በበኩላቸው፤  በተመጣጠነ ምግብ እጥረት የሚቀነጭሩ ሕጻናትን ቁጥር ለመቀነስ ለእናቶች በተግባር የተደገፈ ግንዛቤ የማሳደግ ስራ እየተከናወነ መሆኑን አመልክተዋል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የወረዳው ነዋሪዎች በበኩላቸው የባለሙያዎችን ምክር ተቀብለው እየተገበሩ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ለሕጻነት ልጆቻቸው የተለያዩ የምግብ ዓይነቶችን አመጣጥነው እየመገቡና እያስከተቡ መሆኑን አመልክተዋል።


 

ቀደም ሲል በምዕተ ዓመቱ የልማት ግቦች ተካቶ ቀጥሎም በሰቆጣ ቃል ኪዳን ስምምነት በተመጣጠነ የምግብ እጥረት የሚቀነጭሩ ሕጻናትን ቁጥር ለመቀነስ እንደ አገር ግብ ተቀምጦ እየተሰራ ይገኛል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም