በቤንች ሸኮ ዞን የድልድይ መሠረተ ልማቶች በኅብረተሰብ ተሳትፎ እየተሰሩ ነው

ሚዛን አማን፤ግንቦት 25/2015 (ኢዜአ)፡-በዞኑ በተለያዩ ወረዳዎች ውስጥ የሚታየውን የድልድይ መሠረተ ልማት ችግር በኅብረተሰብ ተሳትፎ ለመፍታት የተጀመረው ጥረት ውጤት እያስገኘ መሆኑን የቤንች ሸኮ ዞን አስተዳደር አስታወቀ።

በዞኑ ለረጅም ጊዜያት ጥያቄ ሆነው የቆዩ የድልድይ መሰረተ ልማት ችግሮችን ለመፍታት ህብረተሰቡን በማቀናጀትና በማሳተፍ የተጀመረው ስራ ተሞክሮ የሚሆን ነው የተባለው።

የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪ እና የፋይናንስ መምሪያ ኃላፊ አቶ ሳሙኤል አሰፋ እንዳሉት በዞኑ የድልድይ መሰረተ ልማት ችግር በስፋት ይታያል።

ይህም አርሶ አደሮች ምርቶቻቸውን በአግባቡ ገበያና በማውጣት የሚጠበቀውን ጥቅም እንዳያገኙ ከመከልከል ባለፈ ለሌሎችም ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ የልማት እንቅስቃሴዎች ተግዳሮት መሆኑን ተናግረዋል።

የአካባቢው ኅብረተሰብ የቅሬታ ምንጭ ከነበሩ የመሠረተ ልማት ጉድለቶች ውስጥ የመንገድና ድልድይ ችግር ቀዳሚ ሲሆን የሚያመርቱትን የግብርና ውጤት ለገበያ ለማውጣት እንደሚቸገሩ ተናግረዋል።

ችግሩን ለመፍታት አስተዳደሩ በየአከባቢው የማህበረሰብ ተሳትፎን በማጠናከርና በማቀናጀት ስራ መጀመሩን ገልጸው፤ ይህም ተሞክሮ የሚሆን ውጤት እየተገኘበት መሆኑን አስረድተዋል።

ለአብነትም ችግሩ ከሚታይባቸው ወረዳዎች መካከል የደቡብ ቤንች ሼይ ቤንችና ሸኮ ወረዳዎች በህብረተሰብ ተሳትፎ ብቻ የአምስት ድልድዮች ግንባታ ተጀምሮ ሶስቱ ተጠናቅቀው ለአገልግሎት ክፍት መሆናቸውን ገልጸዋል።

ከፍተኛ የሆነ የድልድይ መሰረተ ልማት ችግር ከነበረባቸው አንዱ የሆነው የደቡብ ቤንች ወረዳ በሁለት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ሦስት በኅብረተሰብ ተሳትፎ የተገነቡ ድልድዮችን ማስመረቅ መቻሉን  ተናግረዋል።

በዚህም የቡና፣ ኮረሪማና ሙዝ እንዲሁም ሌሎች የግብርና ምርቶችን ለወረዳ፣ ለዞን እና ለማዕከላዊ ገበያ የሚያልፍበት የሾር ወንዝ ድልድይ ግንባታ ተጠቃሽ ሲሆን በዚህ ወንዝ ላይ ድልድይ መገንባቱ አሁን ላይ በአካባቢው ከፍተኛ የኢኮኖሚ መነቃቃት መፍጠር ችሏል ነው ያሉት።

ይህንን ተሞክሮ በሌሎች ወረዳዎች በማስፋፋት የድልድይ ግንባታ እጥረት እያስነሳ ያለውን ጥያቄ በኅብረተሰብ ተሳትፎ ለመመለስ እየተሰራ ነው ያሉት አቶ ሳሙኤል፤ በሼይ ቤንችና ሸኮ ወረዳ ሂደት ላይ የሚገኙ ሁለት ፕሮጀክቶች ግንባታ መጀመራቸውን ጠቅሰዋል።

የደቡብ ቤንች ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ወልዱ ባቺ  በበኩላቸው የአካባቢው ኅብረተሰብ ለፌች፣ ሾር እና ዘልሚ ወንዞች ድልድይ ግንባታ ከ25 ሚሊዮን ብር በላይ በማዋጣት ሙሉ ወጪ መሸፈኑን ገልጸዋል።

በኅብረተሰብ ተሳትፎ የተገነቡ እነዚህ ሦስት ድልድዮች ከ12 በላይ ቀበሌዎችን እርስ በእርስ እና ከወረዳው ጋር እንዲሁም ከዋናው የዞን መንገድ ጋር ማገናኘት እንደሚችሉም ጠቅሰዋል።

ድልድዮቹ የህዝባችንን ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግር የሚቀርፉ ሲሆን ለአብነትም የሾር ወንዝ ድልድይ ከተመረቀ በኋላ ከ10 በላይ በቡና ኢንዱስትሪ የተሰማሩ ባለ ሀብቶች ወንዙን ተሻግረው ሥራ መጀመራቸውን ጠቁመዋል።

የመንግስትን እጅ በመጠበቅ ፈጣን የመሠረተ ልማት ዝርጋታን ማሟላት ስለማይቻል በመተባበር ልማቶችን በራስ አቅም ከፍ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል።

በወረዳው በማኅበረሰብ ሙሉ ወጪ የተገነባው ሦስተኛ የዘልሚ ወንዝ ድልድይ ትናንት የተመረቀ ሲሆን አምስት ቀበሌዎችን ከወረዳው ጋር የሚያገናኝ ነው ብለዋል።

ከአካባቢው ነዋሪዎች መካከል የዞዞ ቀበሌ ነዋሪ አቶ አዳሙ ጃርሹ በዘልሚ ወንዝ ምክንያት "ከዚህ ቀደም የምናመርተውን ቡና፣ ሙዝና ሌሎች የግብርና ምርቶችን ወደ ገበያ ለማቅረብ እንቸገር ነበር" ብለዋል።

ከወረዳው 11 ኪሎ ሜትር ያህል ርቀት ላይ በሚገኘው የዘልሚ ወንዝ ምክንያት ወላድ እናቶችን ወደ ጤና ተቋም በአምቡላንስም ሆነ በሌላ ተሽከርካሪ ማድረስ የማይቻል እንደሆነ አስታውሰው፤ አሁን ላይ በድልድዩ መገንባት ችግሩ መቀረፉን ገልጸዋል።

ለድልድዩ ግንባታ የአካባቢያቸውን ማኅበረሰብ በማስተባበር የድጋፍ ገቢ የማሰብሰብ ሥራ ሲሰሩ እንደነበርም ነው የተናገሩት።

ሌላው የአካባቢው ነዋሪ አቶ ማርቆስ ከበደ በበኩላቸው በክረምት ወቅት በሚፈጠረው የውሃ ሙላት ምክንያት ወንዙን ተሻግሮ መገበያየትና ማኅበራዊ ግንኙነት መፍጠር እንደማይቻል ተናግረዋል።

ከግንኙነት መፍጠር ባሻገር ምርታቸውን በአግባቡ ለገበያ በማቅረብ የኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለመሆን የሚያስችል ዕድል በራሳችን አቅም ፈጥረን በማስመረቃችን ደስተኞች ነን ሲሉም ተናግረዋል።

በወረዳው በማኅበረሰብ ድጋፍ እየተሰሩ ያሉ የድልድይ ሥራዎችን ተከትሎ በተፈጠረው መነሳሳት ከ30 ኪሎ ሜትር በላይ አዲስ የጥርጊያ መንገድ በዞኑ አስተዳደር መሰራቱም ተመላክቷል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም