14ኛው ከተማ አቀፍ  የኪነ-ጥበብ ፌስቲቫል መካሄድ ጀመረ

180

አዲስ አበባ ግንቦት 25/2015 (ኢዜአ)፦14ኛው ከተማ አቀፍ  የኪነ-ጥበብ ፌስቲቫል በአዲስ አበባ መካሄድ ጀመረ።

ፌስቲቫሉ '' በሥነ- ጥበባት ሕብራዊ መልክ የተዋበች ኢትዮጵያ'' በሚል መሪ ሀሳብ ከግንቦት 25 እስከ 27 ይቆያል። 

በከተማ ደረጃ ለ14ኛ ጊዜ በሚካሄደው ፌስቲቫል የሥነ- ጥበብ እንቅስቃሴዎች፣ የተለያዩ ውድድሮች፣ ዐውደ ርዕይ እና ሥነ-ጥበባዊ ክዋኔዎች እየቀረቡ ይገኛሉ።

የአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ የኪነ-ጥበብ ዘርፍ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ሠርፀ ፍሬስብሐሃት በማስጀመሪያው መርሃ ግብሩ ላይ እንደተናገሩት ፌስቲቫሉ በከተማዋ ያሉትን የኪነ-ጥበብ ሀብቶች አጉልቶ ለማሳየት የሚረዳ ነው።
 

የቢሮው ሃላፊ የከተማዋ ነዋሪ፣ የኪነ-ጥበብ አድናቂዎች እና የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች እንዲሁም መገናኛ ብዙሃንም በፌስቲቫሉ ላይ እንዲታደሙ ጥሪ አስተላልፈዋል።

በፌስቲቫሉ ላይ በከተማዋ የሚገኙ የሥነ- ጥበብ ተቋማት፣ ቴአትር ቤቶች፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሥነ ጥበብ ትምህርት ቤቶች፣ የውጭ ዲፕሎማቶች፣ የሃይማኖት ተቋማት ፣ የኪነጥበብ ባለሙያዎች፣ የአንደኛ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንዲሁም የሙያ ማህበራት ተሳትፈዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም