በንጹህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት እጥረት ለተጨማሪ ወጪና እንግልት እየተዳረግን ነው -- በደብረ ብርሃን ከተማ ነዋሪዎች

83

ደብረ ብርሀን ግንቦት 25/2015 (ኢዜአ)፡-በደብረ ብርሀን ከተማ በንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት እጥረት ለተጨማሪ ወጪና እንግልት እየተዳረጉ መሆናቸውን አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የከተማዋ ነዋሪዎች ገለጹ።

የከተማ አስተዳደሩ የውሃና ፍሳሽ አገልግሎት በበኩሉ ህብረተሰቡ ያነሳው ጥያቄ ትክክል መሆኑን አምኖ ችግሩን ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን አስታውቋል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡ ነዋሪዎች መካከል በደብረ ብርሃነ ከተማ ቀበሌ 06 የሚኖሩት አቶ አበጋዝ ገስጥ እንዳሉት፣ በሚኖሩበት ኡራኤል ሰፈር የመጠጥ ውሃ አስከ 20 ቀን ሳያገኙ የሚጠፋበት ጊዜ አለ።

በዚህም በቀን 20 ሊትር በሚይዝ ጀሪካን ከሌላ አካባቢ አስቀድቶ ለማስመጣት ከነማጓጓዣው አስከ 60 ብር በማውጣት ለወጪና እንግልት እየተዳረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ውሃ ለመቅዳት ከአካባቢያቸው ርቀው ሲሄዱ ሌሊት እንደሚነሱ የገለጹት አቶ አበጋዝ፣ ለውሃ የሚባክነው ጊዜም በመደበኛ ሥራቸው ላይ ጫና እንዳሳደረባቸው ገልጸዋል።

"የመጠጥ ውሃ አቅርቦት እጥረት ለተጨማሪ ወጪና እንግልት ከመዳረግ በላይ ከወንዝ የምንቀዳው ውሃ የጤናም ስጋት በመሆኑ ከተማ አስተዳደሩ አፋጣኝ ምላሽ ሊሰጠን ይገባል" ሲሉም ጠይቀዋል።
 

በከተማው የቀበሌ 07 ነዋሪ አቶ ውብሸት መንግስቱ በበኩላቸው ውሃ ከሌላ ቦታ ገዝተው ለማስመጣት የሚከፍሉት ገንዘብ ካለው የኑሮ ውድነት ጋር ተያይዞ ተጨማሪ ጫና እየፈጠረባቸው መሆኑን ገልጸዋል።

ከወንዝና ከጉድጓድ ተቀድቶ የሚመጣ ውሃ የተበከለ በመሆኑ በእሳቸውና በቤተሰባቸው ጤና ላይ ችግር እየፈጠረ መሆኑን የገለጹት ነዋሪው፣ "በእዚህም ለህክምና ወጪ እየተዳረግን በመሆኑ የሚመለከተው አካል ፈጣን ምላሽ ይስጠን" ሲሉ ጠይቀዋል።
 

የደብረ ብርሀን ከተማ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ እንደውቀቱ መታፈሪያ ስለ ጉዳዩ ተጠየቀው በሰጡት ምላሽ፣ በአንዳንድ የከተማዋ አካባቢዎች የንጹህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግር መኖሩን አምነዋል።

በከተማዋ የተፈናቃዮች ቁጥር መጨመር፣ በተዘረጉ የውሃ መስመሮች ላይ የሚደርስ ጉዳት፣ የግንባታ ሥራዎች መስፋፋትና በውሃ መስመሮችና ቆጣሪዎች ላይ የሚደርስ ዝርፊያ ችግሩ እንዲባባስ አስተዋጽኦ ማድረጉን ገልጸዋል።

ከተማ አስተዳደሩ ችግሩን ለመፍታት እየሰራ መሆኑን ያመለከቱት ሥራ አስኪያጁ፣ "የከተማዋን የውሃ አቅርቦት አቅም የሚያሳድግ የውሃ ማጠራቀሚያ ጋን ግንባታና የውሃ መስመር ዝርጋታ ሥራዎች በ75 ሚሊዮን ብር እየተከናወኑ ይገኛሉ" ብለዋል።

በተጨማሪም ሦስት ጥልቅ የውሃ ጉድጓዶች ቁፋሮ ሥራን በከተማ አስተዳደሩና በኢትዮጵያ ውሃ ቴክኖሎጂ የገንዘብ ድጋፍ ለማስጀመር እንቅስቃሴ ላይ መሆኑን ነው የገለጹት።

በከባድ የውሃ መስመር ላይ ባሉ የውሃ ቆጣሪዎችና ሌሎች መሳሪያዎች ላይ የሚፈጸምን ዝርፊያ ለመከላከልም ችግሩ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ከህብረተሰቡ ጋር በመወያየትና ኮሜቴ በማዋቀር ለንብረቶች ጥበቃ እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል።

የከተማዋን የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግር በጥናት በመለየት የከተማዋን ዕድገት መሰረት ያደረገ ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠትም ህብረተሰቡን ያሳተፈ ኮሚቴ ተቋቁሞ ወደ ተግባር መግባቱን ምክትል ሥራ አስኪያጁ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም