ኢትዮጵያ በተያዘው ዓመት ከሱዳንና ከሶማሊያ የመጡትን ጨምሮ ከ110 ሺህ በላይ ስደተኞችን ተቀብላለች- የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት

133

አዲስ አበባ ግንቦት 25 /2015 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ በተያዘው ዓመት ሱዳንና ሶማሊያን ጨምሮ ከተለያዩ ሀገራት ከለላ ፈልገው የመጡ ከ110 ሺህ በላይ ስደተኞችን መቀበሏን የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት አስታወቀ።

ለስደተኞች የተሟላ አገልግሎት ለማቅረብ በመተማ እና በኩምሩክ አዲስ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ግንባታ መጀመሩን አገልግሎቱ አስታውቋል።

 

የአገልግሎቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሙሉዓለም ደስታ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ኢትዮጵያ ወደ ግዛቷ የሚገቡ ስደተኞችን ከለላ በመስጠት የምትታወቅበትን ታሪክ በማስቀጠል በዚህ ወቅት ከአንድ ሚሊዮን በላይ የውጭ ሀገራት ዜጎችን አስጠልላ እንደምትገኝ ተናግረዋል።

በዚህ ዓመት ብቻ እስካሁን ከ110 ሺህ በላይ ስደተኞችን ከሶማሊያ እና ከሱዳን በግጭት የተፈናቀሉ ዜጎችን ተቀብላ በዓለም አቀፍ መርህ መሰረት አስፈላጊውን ሰብዓዊ ድጋፍ እያቀረበች መሆኗን ነው የተናገሩት።

በተለይም የሱዳንን ግጭት ተከትሎ በአማራ ክልል መተማ፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ኩምሩክ እና በጋምቤላ  በኩል በመቀበል ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

እስካሁን በመተማ ብቻ ከ30 ሺህ በላይ ስደተኞች መካከል የጥገኝነትና የከለላ ጥያቄ ያቀረቡ 6 ሺህ 483 የውጭ ዜጎች ምዝገባ መከናወኑን አብራርተዋል።

ስደተኞችን የተሟላ አገልግሎት ለማቅረብ በመተማ እና በኩምሩክ የመጠለያ ጣቢያ ለመገንባት እንቅስቃሴ መጀመሩን ገልፀው፤ በመተማ 57 ሄክታር በኩምሩክ አራት ሄክታር መሬት ከክልሎች መረከቡን ገልጸዋል።

በግጭት ምክንያት ከሶማሊያ ለመጡ የውጭ ዜጎች በሶማሌ ክልል ዶሎ ዞን ቦኦ ወረዳ ሚርቃን ቀበሌ ክልሉ ባመቻቸው 400 ሄክታር መሬት ላይ አዲስ መጠለያ በመገንባት እስካሁን ከ20 ሺህ በላይ የሚሆኑ ስደተኞች ወደ መጠለያው መግባታቸውን ተናግረዋል።

የተመድ የረድኤት ድርጅቶችን ጨምሮ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ስደተኞችን በመደገፍ በጎ አስተዋፅኦ ቢያደርጉም በሚጠበቀው ልክ ባለመሆኑ ይበልጥ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ጠይቀዋል። 

ስደተኞችን የመቀበልና የማስተናገድ ተግባር ከፀጥታና ደህንነት አኳያ ሊያመጣ የሚችለውን ስጋት ከግምት ውስጥ ባስገባ አግባብ ከፌደራል እና ከክልል መንግስታት ጋር በመናበብ እየተሰራ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ለስደተኞች ከለላ መስጠት ብቻ ሳይሆን ተራማጅ የሆነ ሕግ በማውጣት ስደተኞችና ተቀባይ ማህበረሰቡን ያማከለ የዘላቂ ህይወት ማሻሻያ ፕሮጀክቶችን እየተገበረች መሆኑን ጠቅሰዋል።

ለአብነትም ከአጋር አካላት ጋር በመቀናጀት በሶማሌ ክልል ዶሎ አዶ የሚገኙ ስደተኞችን ዘላቂ የልማት ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የተከናወኑ የመስኖ ልማት ስራዎችን በስኬታማነት አንስተዋል። 

ስደተኞች በአካባቢና በተቀባዩ ማህበረሰብ ላይ የሚያደርሱትን ጫና ለመቀነስ የሚያስችሉ መሰል ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም