በሕገ-ወጥ መንገድ የገቡ ከ148 ሚሊዮን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባድ እቃዎች ተያዙ

92

አዲስ አበባ ግንቦት 25/2015(ኢዜአ):-  በሕገ ወጥ መንገድ የገቡ 148 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ እቃዎች  መያዛቸውን የጉምሩክ ኮሚሽን  አስታወቀ።

ኮንትሮባንድ ዕቃዎቹ የተያዙት በድሬዳዋ ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሲሆን የገቡትም  በህገ ወጥ መልኩ  ከጎረቤት አገር ሶማሊያ መሆኑ ተገልጿል። 

ከተያዙት የኮንትሮባንድ እቃዎች መካከል አልባሳት፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ የመኪና መለዋወጫ፣ የመዋቢያ እቃዎች፣ መድኃኒቶች፣ የምግብ ነክ እቃዎች እና የቤት ውስጥ መገልገያ እቃዎች እንደሚገኙበት ገልጿል።

እቃዎቹ የተያዙት ከሕብረተሰቡ በደረሰ ጥቆማ መሰረት የአገር መከላከያ ሰራዊት ፣የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ እና የጉምሩክ ኮሚሽን ሰራኞች በጋራ ባደረጉት ክትትል መሆኑን አመልክቷል።

የኮንትሮባንድ አዘዋዋሪዎቹ በፀረ-ኮንትሮባንድ ግብረ ኃይሉ ክትትል እየተደረገባቸው መሆኑን ሲያውቁ ተሽከርካሪዎቹን ወደ ጫካ በማስገባት ለመሰወር ቢሞክሩም የተሰማራው ግብረ ኃይል ባደረገው የክትትል ስራ በቁጥጥር ስር ማዋል መቻሉ ተጠቁሟል።

ኮሚሽኑ በዚህ የሕግ ማስከበር ዘመቻ ለተሳተፉ የድሬዳዋ ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሰራተኞች እና አመራሮች፣ለአገር መከላከያ ሰራዊት፣ለኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ እና ለአካባቢው ሕብረተሰብ ምስጋና አቅርቧል።

የኮንትሮባንድ እና ሕገወጥ ንግድ ስልቱ ተለዋዋጭ በመሆኑ ድርጊቱን ለመግታትና በአገር ኢኮኖሚ የሚያሳድረውን ተጽእኖ ለመከላከል ሁሉም ባለድርሻ አካላትና ሕብረተሰቡ የበኩሉን እንዲወጣም ጥሪ አቅርቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም