በመጨረሻው ሩብ ዓመት የሚፈጸሙ ግዥዎችን ለማስቀረት የሚረዳ አሰራር ከቀጣዩ ዓመት ጀምሮ ተግባራዊ ይደረጋል

227

አዲስ አበባ ግንቦት 25/2015(ኢዜአ)፡- በመንግሥት ተቋማት በመጨረሻው ሩብ ዓመት የሚፈጸሙ ግዥዎችን ለማስቀረት የሚረዳ አሰራር ከቀጣዩ ዓመት ጀምሮ ሙሉ በመሉ ተግባራዊ እንደሚሆን የመንግሥት ግዥና ንብረት  ባለሥልጣን አስታወቀ።   

የመንግሥት ግዥና ንብረት ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሀጂ ኢብሳ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንዳሉት፤ ተቋማት የሚፈጽሙት ግዥ ባመዛኙ ያልታቀደና በአራተኛው ሩብ ዓመት ላይ ያተኮረ ነው።

አራተኛ ሩብ ዓመት ላይ የሚፈጸሙ ግዥዎች ለመልካም አስተዳደር ችግሮች የመጋለጥ ዕድላቸው ሰፊ እንደሆነና "90 በመቶ የሚሆነው የኦዲተሮች ግኝት ተቋማት በመጨረሻው ሩብ ዓመት ከሚፈጸሙት ግዥ ጋር የተያያዘ ነው" ነው ያሉት። 

እንደ አቶ ሀጂ ገለጻ ተቋማት ምን መግዛት አለባቸው፣ መቼ ነው የሚገዛው፣  ከየት ነው የሚገዛው ፣  የጨረታ ሂደቱ እንዴት ይሆናል ፣ በሚለው ዙሪያ አቅዶ በመስራት በኩል ሰፊ ክፍተት እንደሚስተዋል ነው ያስረዱት።   

ከስልጠናዎች ጋር በተያያዘም ተቋማት የስልጠና መርሃ ግብሮችን በበጀት ዓመቱ መጀመሪያ ወይም በሐምሌ ፣ ነሃሴና መስከረም የዝግጅት ምዕራፍ ማካሄድ ያለባቸው ቢሆንም ይሄ እየተተገበረ አይደለም ሲሉ ነው የገለጹት።     

65 በመቶ የሚሆነው የአገሪቷ በጀት የሚውለው ግዥ ላይ መሆኑን ጠቁመው በጀቱ በዕቅድ ላይ ተመስርቶ በአግባቡ ጥቅም ላይ ካልዋለ በአገርና ሕዝብ ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ከፍተኛ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።   

በመጨረሻው ሩብ ዓመት ተቋማት የሚገዙበት ሥርዓት ከቀጣዩ ዓመት ጀምሮ እንደማይኖር የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ ያልታቀዱ ግዥዎችን ለማስቀረት የመንግሥት ኤሌክትሮኒክ ግዥ ሥርዓት ወሳኝ በመሆኑ በ2016 ዓ.ም በሁሉም የፌደራል ተቋማት ይተገበራል ብለዋል።  

እስካሁን 74 ተቋማት በኤሌክትሮኒክስ ግዥ ሥርዓት የታቀፉ ሲሆን ቀሪ 95 ተቋማት የግዥ ሥርዓቱን እንዲቀላቀሉ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል። 

ለዚህም ይረዳ ዘንድ የመንግሥት ኤሌክትሮኒክስ ግዥ ሥርዓት እንዴት ነው የሚሰራው፣ምን ያስፈልጋል፣ በሚለው ላይ ለተቋማት ባለሙያዎችና አመራሮች ስልጠና እንደሚሰጥም አክለዋል።

የኤሌክትሮኒክስ ግዥ ሥርዓት ተግባራዊ ሲሆን ጥቃቅን እና አስገዳጅ ግዥዎችን ብቻ በአራተኛው ሩብ ዓመት ተቋማት እንዲገዙ ይፈቀዳል ብለዋል።  

በኤሌክትሪኒክስ ግዥ ሥርዓት በአሁኑ ወቅት 15 ሺህ አቅራቢዎች መኖራቸውን የገለጹት አቶ ሀጂ ስርዓቱ በቀጣዩ ዓመት ሁሉም የፌደራል ተቋማት በሂደቱ ስለሚካተቱም አቅርቦቱን የሚመጥን ስራ እየተሰራ ነው። 

ለዚህም ይረዳ ዘንድ በ2016 ዓ ም የአቅራቢዎችን ቁጥር ወደ 32 ሺህ ከፍ ለማድረግ በምዝገባና ስልጠና በመስጠት ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም አብራርተዋል።  

 

       

 

   

 

 

 

                           

 

 

 

         

 

 

 

 

 

 

 

         

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም