የረቂቅ ሙዚቀኛዋ መናኒት ሲታወሱ

የረቂቅ ሙዚቀኛዋ መናኒት ሲታወሱ   

አየለ ያረጋል            

መንደርደሪያ...

እማሆይ ጽጌማርያም 'ዓለም በቃኝ' ብለው በምንኩስና ሕይወት መንነዋል። በቅድመ ምነናም ሆነ ድሕረ ምነና ሕይወታቸው ግን በረቂቅ ሙዚቃ ከመራቀቅ ቦዝነው አያውቁም ነበር። ለዚህ ነው 'የረቂቅ ሙዚቃ ተራቃቂዋ መናኒት' የሚሰኙት።

በእማሆይ ጽጌማርያም ገብሩ ፋውንዴሽን ድጋፍ ሰሞኑን በእንጦጦ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ 'ዝክረ እማሆይ ጽጌማርያም' መርሐ ግብር ተደርጎ ነበር። የቀድሞ ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ተማሪዎች መርሐ ግብሩን አሰናድተዋል። 

በሕይወት ዘመናቸው ከ300 በላይ የረቂቅ ሙዚቃ ስራዎችን ለአድማጭ ጆሮ ያበረከቱት እማሆይ ጽጌማርያም ያረፉት ባሳለፍነው መጋቢት 22 ቀን 2015 ዓ.ም ነበር። ስርዓት ቀብራችው የተፈጸመውም ለ40 ዓመታት በገዳማዊ ሕይወት በኖሩባት ሀገረ-እስራኤል ኢየሩሳሌም ነው። 


 

የእንጦጦ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የሙዚቃ ትምህርት ክፍል ስያሜውን 'እማሆይ ጽጌማርያም የሙዚቃ ትምህርት ክፍል' በሚል ሰይሟል። እኛም እማሆይን በወፍ በረር መዘከር ወደድን!!

የ'የውብዳር' ሙዚቃ ልክፍት

ሙዚቃ ኅይል ነው-ውስጥን የሚፈነቅል፤ መንፈስን የሚሰረስር። የየውብዳር የሙዚቃ ውበትና ቃና ልክፍትም በዘመነ ደቂቅነት የተጸነሰ ነው። የሙዚቃ ፍቅራቸው ጠሊቅ፣ ስራቸውም ረቂቅ ነው። ግና በጨቅላነት የ'ግዳይ ጣይ' አዳኞችን ባህላዊ ዜማ ተከትለው ሮጠዋል። በቤተ ክርስቲያን ማህሌታዊ ዜማዎች ቀልብና ልባቸው ተማርኳል። የልጅነት ዕዝነ ልቦናቸው በሙዚቃ ቃና ተለክፏል። የደቂቅነት ዐይነ ልቦናቸው ተፈጥሯዊ ውበት በረቂቅ ሙዚቃ እንዲራቀቁ ሰበብ ሆኗቸዋል። 'ከሰፈር እስከ ማዶ-ሀገር' ኑረታቸው በዕዝነ ልቦናቸው ያቃጨለ የድምጽ ርግብግቢት በረቂቅ ሙዚቃ እንዲመንኑ መሰረት ሆኗቸዋል። የየውብዳር ዑደት ሕይወት ከዓለማዊ ወደ ሰማያዊ ሕይወት ብቻ ሳይሆን በመሳሪያ ወደ ተቀነባበሩ ረቂቅ ሙዚቃ ዳርቻም መንኗል። የወላጅ እናታቸው ካሳዬ የለምቱ በገና ደርዳሪነት፣ የአባታቸው ከንቲባ ገብሩ ደስታ የረቂቅ ሙዚቃ አጣጣሚነት በሙዚቃ ጣዕም የመለከፋቸውን ልክ አንሮታል። ሙዚቃን "የስሜት መግለጫ ቋንቋዬ፤ የሀዘንና ደስታዬ ጓድ” ይሉታል-የኋላዋ እማሆይ ጽጌማርያም፤ የያኔዋ የውብዳር ገብሩ!


 

እማሆይ ጽጌማርያም ውልደታቸው ከደህና ቤተሰብ መደብ ነው። አባታቸው ከንቲባ ገብሩ ደስታ በዘመናዊት ኢትዮጵያ ታሪክ ጉልህ አሻራ አላቸው። ዕውቁ የታሪክ ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ ከንቲባ ገብሩ ደስታን ከ20ኛው ከፍለ ዘመን የኢትዮጵያ ዘመናዊ ትምህርት ፋናወጊዎች መካከል አንዱ ናቸው ይሏቸዋል። በአጼ ቴዎድሮስ ዘመነ መንግስት በጣና ሐይቅ ምዕራባዊ ዳርቻ አለፋ ጣቁሳ የተወለዱት ገብሩ ደስታ ገና በልጅነታቸው በሚሲዮናዊያን ጋር ወደ ኢየሩሳሌም ተወስደው የተማሩ፤ በተለያዩ ሀገራት ተዘዋውረው ያስተማሩና በኋላም ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው ከአጼ ዮሐንስ እስከ አጼ ኅይለስላሴ ዘመነ መንግስት ሀገራችውን ያገለገሉ ጎምቱ ባለታሪክ ናቸው። ከንቲባ ገብሩ ደስታ የሀረር እና የጎንደር ከንቲባ፤ በአሜሪካና በአውሮፓ ሀገራት የዲፕሎማቲክ ልዑክ መሪ፣ የመጀመሪያው ሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባዔ በኋላም ዋና አፈ ጉባዔ ነበሩ። ከንቲባ ደስታ በየዘርፋቸው ኢትዮጵያን ያገለገሉ ልጆችን በእግራቸው ተክተዋል። ኮሎኔል ዳዊት ገብሩ፣ ገነት ገብሩ፣ ደስታ ገብሩ፣ የውብዳር ገብሩና ስንዱ ገብሩ ተጠቃሽ ናቸው። የውብዳርም የሕይወት ውጣውረድና አቀበት አልፈው፤ መክሊታቸውን ፈልገው የኖሩ ተምሳሌታዊ መናኒት ሆነዋል።


 

ልደታቸው ታኅሣሥ 13 ቀን 1916 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ነበር። ገና በ6 ዓመታቸው በኋላ የጦር አርበኛ፣ ፀሐፊ ተውኔት፣ ደራሲ፣ የመጀመሪያዋ ሴት የፓርላማ ተመራጭና ዲፕሎማት ከነበሩት ታላቅ እህታቸው ስንዱ ገብሩ ጋር ስዊዘርላድ ለትምህርት አቀኑ። የውብዳር ወደ የባሕር ማዶ ጉዟቸውን ሲያስታውሱ "ከጅቡቲ ጉዞ በጀመርንበት ጀልባ ላይ የተሳፈርን ብቸኛዎቹ ጥቁሮች እኛ ነበርን። በዚያ ድቅድቅ ጨለማ ሰማዩ ላይ የፈካችውን ሙሉ ጨረቃና ማዕበል የሚንጠውን ባህር በተመስጦ ነበር የምመለከተው። ከዚያ በመነሳት በኋላ ላይ “የባህር ላይ ዘፈን- Song of the sea' የሚለውን ሙዚቃ ደረስኩ" ብለው ነበር። የተፈጥሮን ውበት ልክ በሙዚቃ ኅይል በመግለጥ የተካኑ ጠቢብ ናቸውና ገጠመኛቸውን በረቂቅ ሙዚቃ ተራቀቁበት።

በስዊዘርላንድ 'ሞንትሚሬል ትምህርት ቤት' በዕድሜ ትንሿ ተማሪ ነበሩ። አንድ ዕለት የቫዮሊን ድምፅ ሰምተው ተማረኩና መጫወት ጓጉ። በሌላ ዕለት አንዲት ፒያኖ አግኝተው ቁልፉን በጣቶቻቸው እየደቆሱ ምስቅልቅል ስሜታቸውን አስተጋቡበት። ሙዚቃውንም 'ማዕበል' ብለውታል። እናም ከቀለም ትምህርቱ በተጓዳኝ ቫዮሊንና ፒያኖ አጠኑ።ገና በ10ኛ ዓመታቸው የመጀመሪያ የሙዚቃ ትርዒት አቀረቡ።

“ከንቲባ ገብሩ የኢትዮጵያ ባለውለታ” በተሰኘው የወንድማቸው ኮሎኔል ዳዊት ገብሩ መጽሃፍ ውስጥ የተጠቀሰው የእማሆይ ጽጌማርያም ማስታወሻ "... በሰባት እና በስምንት ዓመት ዕድሜዬ፣… ከሥነ ፍጥረት ጋር ወዳጅነት ነበረኝ፡፡ አበቦች ውብ ልዕልቶች፣ ዛፎች… እንደ ዘበኞቻቸው፣ ነፋስ… ወጣት መልዕክተኛ፣ ፀሐይ… ደግሞ የዓለም ኹሉ ንግሥት ኾነው ይታዩኝ ነበር፡፡  ያን ጊዜ በአዳሪ ትምህርት ቤቱ ውስጥ በኔ ዕድሜ ልጅ ስላልነበረ…ብቸኝነት የሕጻንነት ጓደኛዬ ኾኖ አብሮኝ አደገ፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ አንድ የኀዘን ስሜት፣ የመንፈስ ዕረፍት ዕጦት አደረብኝ፡፡ ሙዚቃ እወድ ነበርና ስሰማው የኀዘን ስሜት ያመጣብኝ ነበር" ይላል።


 

የፒያኖ ትምህርታቸውን አዲስ አበባ ተመልሰው በእቴጌ መነን አዳሪ ትምህርት ቤት አጠናክረዋል። ልምምዳቸው ግን በጣሊያን ወረራ ምክንያት ተቋረጠ። የ13 ዓመት ልጃገረድ ነበሩ። በፋሺስት ኢጣሊያ ጦር ከነቤተሰቦቻቸው በፖለቲካ እስረኛነት ወደ ኢጣሊያ አሲናራ ደሴት ወህኒ ቤት ተጋዙ። በግዞት ሆነው ግን ከካቶሊክ ሲስተሮች ጋር ኦርጋን ይጫወቱ ነበር። ሙዚቃ ልክፍታቸው ነውና!!

ከሶስት ዓመት ግዞት በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ቢመለሱም የሙዚቃ ቃና ልክፍታቸው ግን ወደ ውጭ ሀገር ተመልሶ የመማር ጉጉታቸው ናረ። እናም ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የጸሃፊነት ስራቸውን አቋርጠው የትምህርት ዕድል ተፈቅዶላቸው ወደ ግብጽ ካይሮ አመሩ። በካይሮ ቆይታቸው “ቬሉኑስ ኮንሰርቫቶሪ ኦፍ ሉቺኒያ” በተሰኘ የሙዚቃ ትምህርት ቤት ቫዮሊንና ፒያኖ ተምረው ዲፕሎማ ተቀበሉ። "በየዕለቱ ቫዮሊን ለአራት ሰዓታት፤ ፒያኖ ደግሞ ለአምስት ሰዓታት ያህል እጫወታለሁ። በየመሃሉ ደግሞ ወደ ሬስቶራቶችና ፊልም ቤቶች እየሄድኩ እዝናና ነበር" ብለዋል በአንድ ወቅት ለቢቢሲ በሰጡት ቃለ ምልልስ። በካይሮ ሙቀት ምክንያት ወደ አዲስ አበባ እስኪመለሱ ድረስ የሙዚቃ ናፍቆታቸውን በቅጡ አጣጠመዋል።

የውብዳር የሙዚቃ ጥማቸውን አልቆረጡም። አውሮፓ ተሻግሮ የመማር ፍላጎታቸው አልተቋረጠም። በእንግሊዝ ነፃ የሁለት ዓመት የትምህርት ዕድል ቢያገኙም ሳይፈቀድላቸው ቀረ። ክፉኛ አዘኑ። ከከባድ ህመምና ድባቴም በህክምና ዳኑ። በሂደትም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ውብ ዝማሬዎች እየተሳቡ መጡ። የሙዚቃ ትምህርት ምናኔያቸው ወደ መንፈሳዊ ሕይወት ምናኔ ተለወጠ። ውሎ አዳራቸው ቤተ መቅደስ ሆነ። ".... የዚህ ዓለም ፍቅር እና የመኖር ፍላጎት ከኅሊናዬ ፈጽሞ ተወገደ" ብለዋል በማስታወሻቸው።

ከ'የውብዳር ወደ 'እማሆይነት' ምናኔ 

በወቅቱ የ19 ዓመት ልጅ ነበሩ። በአንድ ዕለት ወጣቷ የውብዳር ለንግስ በዓል ከአዲስ አበባ ወሎ ግሸን ማርያም ተጓዙ። ለሁለት ዓመታት ሰዓታትና ቅዳሴ ሳያቋርጡ ተማሩ፤ ፀለዩ። ታሪክን እንዲህ ያወሳሉ። “…ሁሉንም ነገር ዕርግፍ አድርጌ ትቼ ከዓለም ተነጠልኩ። እቅዴ በጫካ ውስጥ ባህታዊ ሆኜ ኑሮን ለመግፋት ነበር። ግሸን ማርያም እንደደረስን መነኮሳቱን ቀሳውስቱንና አቡነ ሚካኤልን አገኘሁ። ለመመንኮስ እንደመጣሁ ለአቡነ ሚካኤል ነገርኳቸው። እርሳቸው ግን ፈቃደኛ አልነበሩም። እኔም ውሳኔዬ መሆኑን አስረግጬ ነገርኳቸው.... በሀሳቤ የፀናው መሆኑን ካረጋገጡ በኋላ ተስማሙ" ይላሉ። 


 

እናም መስከረም 21 ቀን 1940 ዓ.ም. በ20ዎቹ ዕድሜያቸው መጀመሪያ ለማዕረገ ምንኩስና በቁ። 'የውብዳር' የተሰኘው ስማቸው በክርስትና ስማችው እማሆይ ጽጌማርያም ተቀየረ። እማሆይ ሙሉ ጊዜያቸውን ለሙዚቃ ቅማሬ እና መንፈሳዊው ግልጋሎት ሰጡ። "... ሙዚቃውን እንዳላጣው ፈለገ። ሁሉም በእርሱ ሞገስ ነው የሆነው" ይላሉ። ለአስር ዓመታት በግሸን ማርያም ገዳም ያለ ጫማ ተጉዘዋል። 

እማሆይ ፅጌማርያም በመንፈሳዊ ሕይወትም፤ በረቂቅ ሙዚቃም መንነዋል። የሙዚቃ ስራዎቻችውም ከአፍሪቃ ቀንድ አልፎ በምዕራቡ ዓለም ናኝቷል። ስራዎቻቸውም ታዲያ ከመንፈሳዊ ተመስጦ ባሻገር ለሰብዓዊ ርዳታ ተልዕኮ የሚውል ነበር። እማሆይ ጽጌማርያም ከመጀመሪያ አልበማቸው ጀምሮ ከአልበም ሽያጭ የተገኘ ገቢ ለግላቸው ተጠቅመው እንደማያውቁ ይነገራል፤ ለህጻናት እርዳታ ያውላሉ እንጂ። “በደርግ ዘመን ከታተመው አራተኛ አልበሜ ያገኘሁትን ገንዘብም ኢየሩሳሌም ውስጥ ያለችውን የኪዳነ ምህረት ቤተክርስቲያን ለመደገፍ አዋልኩት። ዘቪዥነር ከተሰኘው አልበሜ ያገኘሁትን ገንዘብም በወቅቱ የገንዘብ ድጋፍ ለማግኘት ከወዲያ ወዲህ ይል ለነበረው ኢጂኤም ፋውንዴሽን ድጋፍ አድርጌበታለሁ። ሶቨኔርስ የተሰኘ ስድስተኛ አልበሜ የተገኘው ገቢም በኢየሩሳሌም ለሚገኝ ቤተክርስቲያን ድጋፍ የሚውል ነው” ብለዋል እማሆይ። 


 

ሙዚቃ በሸክላ ለማስቀረጽ የወሰኑትም በጎንደር በነበሩበት ወቅት ከቅዳሴ መልስ ባጋጠማችው ክስተት እንደነበር እንደህ አውስተዋል። "ጎንደር በነበርኩበት ጊዜ በየቤተክርስቲያኑ የማይጠገበውን ማኅሌት ሰምቼ ስመለስ፤ እደጅ የአገር ቤት ተማሪዎች በየሜዳው ጥቅልል ብለው ተኝተው አያለሁ፡፡ ብጠይቅ ሌሊት ቤተክስቲያን ያደሩ ናቸው፣ ቤት የሌላቸው፡፡ በዚህም ልቤ ተነካ፣ አዘንኩ፡፡ እኔ ሀብት የለኝ፤ ያለችኝ ያቺው ሙዚቃዬ፡፡ ስለዚህ እስኪ ሙዚቃዬን ላስቀርጽ እና ሽያጩን እነዚህ ልጆች ገብተው በነጻ የሚያድሩበት ቤት ላቋቁም አልኩ" ይላሉ።

እማሆይ ጽጌማርያም እስከ ሕልፈተ ሕይወታቸው ድረስ ለአራት አስርት ዓመታት ገዳማ ኑሯቸውን በሀገረ-እስራኤል ኢየሩሳሌም በሚገኙ የኢትዮጵያ ገዳማት አድርገው ቆይተዋል።

'የፒያኖዋ እመቤት' ረቂቅ አሻራዎች 

እማሆይ ጽጌማርያም የአንድ ምዕተ ዓመት ምድራዊ ሕይወት ዘላለማዊ አይረሴ ስራዎች አቅርበዋል። በፒያኖ ረቂቅ ሙዚቃ ቅማሬያቸውም 'የፒያኖዋ እመቤት' የሚል ስም አትርፈዋል። እማሆይ ጽጌማርያም ከዓለማዊ ወደ መንፈሳዊ ሕይወትን የዘነቁ፣ ሀገርኛ ወደ ባህር ማዶ ረቂቅ ጥበብን አዋህደው የተራቀቁ፣ የፒያኖ ቀማሪ፣ የቫይሊን ደርዳሪ፣ የኖታቸው ቃና መንፈስን ኮርኳሪ፣ ስክነትና ጥልቅ ተመስጦን መካሪ፣ መክሊታቸውን የኖሩ፣ በስራዎቻቸው አድማስ ዘለል አድናቆትና ሞገስ የተቸሩ፣ ... የረቂቅ ሙዚቃ እመቤት ናቸው። 

የኢትዮጵያን ሙዚቃ ለመጀመሪያ ጊዜ በጀርመን ሀገር በሸክላ ካስቀረጹት ነጋድራስ ተሰማ እሸቴ ቀጥሎ እማሆይ ፅጌ ማርያምም የኢትዮጵያን ክላሲካል ሙዚቃዎች በሲዲ በማስቀረፅ ለዓለም ሕብረተሰብ ያስተዋወቁ የመጀመሪያዋ እንስት ናቸው። በአጠቃላይ ስድስት የሙዚቃ አልበሞችን አሳትመዋል። በ1955 ዓ.ም. “ሆምለስ ወንደረር-ቤት አልባ መንገደኛ” እና “ሶንግ ኦፍ ዘ ሲ-የባሕሩ ዜማ” ሁለት አልበሞች ጀርመን ውስጥ አስቀርጸዋል። ዕውቁ የሙዚቃ ሊቅ ሞዛርት በተጫወተበት ፒያኖ የመጫወት ዕድል ገጥሟቸዋል። የቤቶቨንን፣ የሞዛርትንና ሽትራውዝን ጨምሮ የአያሌ ክላሲካል ሙዚቃ ሊቆችን ስራዎች ተጫውተዋል።


 

ከ1950ዎቹ መጀመሪያ ጀምሮ የሙዚቃ ኮንሰርቶችን አቅርበዋል። በኢየሩሳሌም ሁለት ኮንሰርቶች አቅርበዋል። ስራዎቻቸው 'ኢትዮፒክስ' በተሰኘው የፈረንሳዊው አቀናባሪ  ፍራንሲስ ፋልሴቶ ተከታታይ የሙዚቃ አልበሞች ውስጥ ተካተዋል። የእማሆይ ጽጌማርያም ሙዚቃ 'ፓሲንግ' የተሰኘው የሆሊውድ ፊልም እና የፔጆ መኪና ማስታወቂያን አጅቧል።

እማሆይ ስራዎቻቸውና ስብዕናቸውም የተጣጣመ ነው። በ1950 ኮንሰርታቸው በወሎ ረሀብ አደጋ ተጎጂ ዜጎች ድጋፍ ለማሰባሰብ ታልሞ በተዘጋጀው ኮንሰርት ላይ የቬትሆንን 'ፓቲክ' እና 'ሆምለስ ወንደረር' የተሰኘ ስራዎች ተጫውተዋል። ወደ ወሎ ሂደው በርሀብ አለንጋ የተገረፉ ህጻናትን በአካል በማየት ‘የድርቅ እልቂት-famine disaster' የተሰኘ ሙዚቃ ደርሰዋል። 

የፒያኖዋን እመቤት ሥራዎች ለቀጣይ ትውልድ ለመዘከር የተቋቋመው 'የእማሆይ ጽጌማርያም ፋውንዴሽን' በረቂቅ የሙዚቃ ዘርፍ ዕድገት የበኩሉን ሚና ሲጫወት ቆይቷል። በእማሆይ የሙዚቃ መንበር ለመቀመጥና ለረቂቅ ሙዚቃ መራቀቅ የሚሹ ወጣቶችን ይደግፋል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት እና በእንጦጦ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ስር በሚገኘው የሙዚቃ ትምህርት ክፍል ፒያኖን ጨምሮ ለሙዚቃው እምርታ የሚያግዝ ቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል። ለዓመታት ሲገለገሉበት የነበረው ፒያኖም ለያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት እንዲሰጥ በመናዘዛቸው በቅርቡ ለትምህር ቤቱ ተሰጥቷል።

ከሕልፈተ ሕይወታቸው በኋላ “ኢየሩሳሌም” የተሰኘ 10 የፒያኖ ትራኮች የያዘ አልበማቸው በሚሲሲፒ ሪከርድስ አማካኝነት እንደሚወጣ ተገልጿል። እማሆይን የሚዘክሩ መፃሕፍት በተለያዩ ወገኖች ታተመዋል፤ ጥናትና ምርምር ስራዎችም እየተሰሩ ነው።

እማሆይ በሙዚቃ ጠበብቶች ሲዘከሩ...

እማሆይ አራቱን የኢትዮጵያ ቅኝቶች በአንድ ድርሰት በመቀመማቸው የሙዚቃ ጠበብት ያደንቋቸዋል። ከሰሞኑ "የፒያኖዋ እመቤት" እማሆይ ፅጌማርያም ገብሩ በሕይወት ዘመናቸው ለኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ ኢንዱስትሪ ዕድገት የነበራቸውን አበርክቶ የሚዘክር መርሐግብር በእንጦጦ ፖሊ-ቴክኒክ ኮሌጅ ሲካሄድ በርካታ ታዋቂ ሰዎችና የኪነ ጥበብ ሰዎች ታድመው ነበር።

የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ፕሬዚዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን እማሆይ ጽጌማርያም በጠላት ወረራ የአርበኝነት ዘመን ክፉውን ጊዜ የቀመሱ፣ ሕይወታቸውም አልጋ ባልጋ ሳይሆን በውጣ ውረድ የተሞላ፣ በሀገር አንድነትና በኅይማኖት በጽኑ የሚያምኑ እንደሆኑ ገልጸዋል። "የሙዚቃ ስራዎቻቸው ፍትህን፣ አንድነትን፣ መንፈሳዊነትን እና ሰላምን የሚገልጹ ናቸው። የእማሆይ የሙዚቃ ስራ በተጨነቅን ጊዜ ስናደምጥው መንፈስ የሚያረጋጋ ሕያው ስራ ነው፤ ተማሪዎች ፈለጋቸውን እንደሚከተሉ ተስፋ አደርጋለሁ" ሲሉ ተደምጠዋል።


 

የቀድሞ ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ተማሪዎች ሰብሳቢ አንጋፋው አርቲስት ደበበ እሸቱ "የእማሆይ ጽጌማርያም ስራ በወረቀት ተጽፎ የሚቀር ሳይሆን በልብና በአዕምሯችን ታትሞ የሚቀር ነው" ሲሉ ገልጸውታል። በረቂቅ ሙዚቃ አጨዋውታቸው ዓለምን ያስደነቁ፤ የህያው ስራ ባለቤት እንደሆኑም እንዲሁ።

በእንጦጦ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ የሙዚቃ ባለሙያው በላይ አለማየሁ እማሆይ ጽጌማርያም "ዘመናዊ ሙዚቃ ባልተለመደበት ዘመን አዲስ የሙዚቃ ስነ ዘዴ ያመጡ፤ የሙዚቃ ስራዎቻቸውም ኢትዮጵያዊውን ቃና ከአውሮፓ ሙዚቃ በማዋሀድ በሁለት ቅኝቶች ውህደት አዲስ ፈጠራ ያመጡ፣ የሙዚቃ ዕውቀታቸው የሚያስደንቅ፣ ዋጋ ከፍሎ ህልምና ማሳካት እንደሚቻል በሙዚቃ ልህቀት ላይ በመድረስ በተግባር ያሳዩ የጥበብ ሰው፣ ለሙዚቃው ዘርፍ ተግባራዊ ምሳሌ ናቸው" በማለት ይገልጸዋቸዋል።

የሙዚቃ ትምህርት ክፍል አሰልጣኟ ዊንታና ንጉሴ በበኩሏ "እማሆይ በኢትዮጵያ ሙዚቃ ታሪክ ትልቅ ሚና የተጫወቱ ስራዎቻቸውም የሚዘከሩ ናቸው፤ እንደ ሙዚቃ መምህርነቴም አርዓያዬ ናቸው" ትላለች።  በእማሆይ ጽጌማርያም ስራዎች ላይ የመመረቂያ ስራዋን ያዘጋጀቸው ሰዓሊና ዲዛይነር ሀበሪ እጅጉ በበኩሏ "እማሆይ ምድራዊና ሰማያዊ ሕይወት አቻችለው የኖሩ፤ ሁለት ድል ያሳዩ ናቸው። ጥቁር ኢትዮጵያዊ ሆነው በዓለም የታወቁ፣ ለዓላማችው ስኬት ትልቅ ተጋድሎ ያደረጉ፣ በመክሊት መኖርን የሚያስተምሩ እናት" ትላቸዋለች።

የኢትዮ ጃዝ አባት የሚሰኘው አንጋፋው ሙዚቀኛ ሙላቱ አስታጥቄ ከወራት በፊት ለቢቢሲ በሰጠው ቃለ መጠይቅ "እማሆይ በእውነት እጅግ የማደንቃቸው እና የማከብራቸው ታላቅ ባለሞያም፤ ታላቅ ሰው ናቸው። ለኢትዮጵያ ሙዚቃ ትልቅ ሥራ ሰርተዋል.... የእማሆይ ጽጌ ማርያም ሥራ ተጠንቶ በየትምህርት ቤቱ እንዲቀመጥ፣ እንዲጠና ማድረግ የግድ አስፈላጊ ነው ብዬ አምናለሁ። የሙዚቃ ትምህርት ካሪኩለም ውስጥ እንዲገባ እና ወጣቶቹ እንዲማሩት ማድረግ ያስፈልጋል" ይላል። 

ዕውቁ የሙዚቃ ባለሙያ ሃያሲ ሰርፀ ፍሬስብሃት በአንድ ወቅት በፃፈው መጣጠፍ እማሆይ ጽጌ ማርያም ገብሩ በክላሲካል ሙዚቃ ዘርፍ በብቸኛ የሙዚቃ ቀማሪነት እና ፒያኒስትነት ጉልህ የታሪክ ቦታ እንደያዙ ገልጿል። "እማሆይ ጽጌ ማርያም በሙዚቃ ምክንያት ብዙ ተፈትነዋል፡፡ ከመንፈሳዊ ሕይታቸው ጋር የሚቃረን የሚመስላቸው አንዳንዶች፣ ሙያቸውን እና የሙዚቃ ፍቅራቸውን አጣጥለውባቸዋል፡፡  የሕይወታቸውን አቅጣጫ ፍጹም በማይገመት መንገድ እንዲጓዝ ያደረገም ነው፡፡ ከሀገራቸው አሰድዶ ተነጥለው እንዲኖሩ ያደረገ ነው፡፡ ግን ከዚህ ኹሉ በኋላ የስማቸው ትንሣኤ፣ ከዘጠኝ ዐሥርት ዓመታት በኋላ በታላቅ ክብር ለብዙዎች ታይቷል" ብሏል፡፡ 

እማሆይ ራሳቸውም "አንዳንድ ሰዎች ይቃወሙታል። ነገር ግን ሁሉም ነገር በእግዚአብሔር ፈቃድ ነው የሚሆነው። ይሄ የክላሲካል ሙዚቃ ነው። እግዚአብሔርንም በተለያዩ የሙዚቃ መሳሪያዎች ማወደስ ይቻላል" ሲሉ ለቢቢሲ ራዲዮ ፎር ተናግረዋል።

ሰሞን ታዋቂው ጋዜጣ ኒወርክ ታይምስ "ባለልዩ ተስጥኦ ኢትዮጵያዊ መነኩሲት" በሚል ሰፊ ሀተታ ጽፏል። በዚሁ ጋዜጣ ላይ ኖራ ጆንስ የተባለ ሙዚቀኛ "የእማሆይ አልበም እስካሁን ከሰማኋቸው ውብ ሙዚቃዎች ሁሉ የላቀ ስራ ነው" ሲል አድንቆታል።

እስራኤላዊት ሙዚቀኛ ማያ ዱኔትዝ እማሆይ "የምዕራቡን ዓለም ረቂቅ ሙዚቃ ከኢትዮጵያዊ ባህላዊ ሙዚቃ ቅርስ ጋር በመቀመር ለዓለም ጆሮ አዲስ ድምጽ አፍልቀዋል። …ሙዚቃዎቻቸው በስፋት መንፈሳዊ መልክ አላቸው። የእማሆይ ሙዚቃዎች የጥሞና፣ ትህትና፣ የጥልቅ ተመስጦ፣ የሰላማዊ ድባብ፣ አሳዛኝ ግን በፍቅርና በእምነት የተዋጡ ... ድምጾች" በሚል ትገልጻቸዋለች።

እማሆይ ጽጌማርያም የሙዚቃ ኅይል በርግጥም ውስጥን የሚፈነቅል፤ መንፈስን የሚሰረስር መሆኑን በዘመናቸው ሁሉ ከሙዚቃ ጋር ላይነጣጠል  ከህይወታቸው የተጋመደ በሰሯቸው ዘመን አይሽሬ ስራዎች አሳይተውናል። የእማሆይ ጽጌማርያም የአንድ ምዕተ ዓመት ምድራዊ ሕይወት ዘላለማዊ አይረሴ ስራዎች በትውልዱ ውስጥ እንደረቀቁ ይኖራሉ። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም