የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ልዑክ በቻይና ይፋዊ የስራ ጉብኝት እያደረገ ነው

162

አዲስ አበባ ግንቦት 25/2015(ኢዜአ)፦የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የልዑካን ቡድን በቻይና ይፋዊ የስራ ጉብኝት በማድረግ ላይ ይገኛል።

ጉብኝቱን እያደረጉ የሚገኙት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የማርኬቲንግ እና ኮሚዩኒኬሽን መምሪያ ከሌሎች የኮርፖሬሽኑ የስራ ኃላፊዎች ጋር ነው።

በጉብኝቱ ቻይናውያን ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ይበልጥ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ለማስቻል፣ አጠቃላይ የመንግስት የኢኮኖሚ ማሻሻያ ስራዎች ላይና ያሉ ምቹ የኢንቨስትመንት ሁኔታዎችን አስመልክቶ ከባለሀብቶች ጋር ውይይት እየተደረገ መሆኑ ተገልጿል።

የኮርፖሬሽኑ ልዑክ በቻይና የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጉብኝት ያካሄደ ሲሆን በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር ተፈራ ደርበው ጋር ስለ ኢንቨስትመንት ምልመላ ስራዎች እና ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ውይይት አካሄዷል።


 

የተቋሙ የማርኬቲንግና ኮሚዩኒኬሽን መምሪያ ኃላፊው አቶ ዘመን ጁነዲን እና የልዑካን ቡድኑ ስለ ኮርፖሬሽኑ አጠቃላይ የሪፎርም ተግባራትና የስራ እንቅስቃሴ እንዲሁም የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ በ2015 ዓ.ም በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት የተደረጉ ቅድመ ዝግጅቶችንና ለኢንቨስተሮች የተዘጋጁ ምቹ ሁኔታዎችን አስመልክተው ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ልዑኩ በቻይና ቆይታው የተለያዩ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን፣ ነጻ የንግድ ቀጣናዎችንና የኢንቨስትመንት ቦታዎችን እንደሚጎበኝ ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም