ወይዘሪት ፀጋ በላቸውን በመጥለፍ ወንጀል የተጠረጠሩ 11 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው ነው- ቢሮው

ሀዋሳ ግንቦት 25 /2015 (ኢዜአ):- ወይዘሪት ፀጋ በላቸውን በመጥለፍ ወንጀል የተጠረጠሩ 11 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን የሲዳማ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ አስታወቀ።

የሲዳማ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ሃላፊ አቶ አለማየሁ ጢሞቲዮስ ጉዳዩን በተመለከተ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ በተደረገው የተቀናጀ የፀጥታ ኦፕሬሽን በተጠርጣሪው ግለሰብ የተጠለፈች ወይዘሪት ፀጋ በላቸውን ማስጣል መቻሉን ተናግረዋል። 

ግንቦት 15 ቀን 2015 ዓ.ም ከመደበኛ ስራዋ ወጥታ ወደቤቷ ስታቀና ተጠርጣሪው ግለሰብ ከሌሎች ግብረ አበሮቹ ጋር የጠለፋ ወንጀል መፈጸሙን ገልጸዋል። 

ጉዳዩ ለፖሊስ ከደረሰ ጀምሮ ግብረ ሀይል በማቋቋም ወይዘሪት ፀጋ በላቸውን ከተጠርጣሪው ለማስመለጥና ወንጀለኞችን በቁጥጥር ስር ለማዋል የተቀናጀ ክትትል እና ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን ተናግረዋል። 

ለዚሁ አጋዥ የሆነው በሀዋሳ ከተማ የተተከለው የደህንነት ካሜራ ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ገልጸዋል። 

ተጠርጣሪው ከነግብረ አበሮቹ ወደ ምስራቅ ጉጂ ቦሬ ከዚያም ጭሮ፣ ሻፋሞና አለታ ወንዶ ድረስ ወይዘሪት ጸጋን ይዞ አቅጣጫ ለማሳት በሚያደርገው ጥረት የጸጥታ ሀይሉ በልጅቱ ላይ ጉዳት ሳይደርስ በቁጥጥር ስር ለማዋል የተቀናጀ ስራ መስራቱን ተናግረዋል። 

ተጠርጣሪውና ግብረ አበሮቹን ለመያዝ የጸጥታ ሀይሉ ከአከባቢው ማህበረሰብ ጋር በመሆን በተደረገው ጥረት ማምለጥ አለመቻላቸውን ሲረዱ ወይዘሪት ፀጋ በላቸውን መልቀቃቸውን ነው ያብራሩት። 

እስከ አሁን ድረስ ፖሊስ ባደረገው ኦፕሬሽን ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት የነበራቸውና የወንጀሉ ተጠርጣሪ የሆነ 11 ግለሰቦችን ፖሊስ በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ መጀመሩን ተናግረዋል። 

አሁን ላይ ወይዘሪት ፀጋ በላቸው በመልካም ጤንነት ላይ እንደምትገኝ የገለጹት አቶ አለማየሁ በቀጣይ የማረጋጋትና የጤና ምርመራና ከተደረገላት በኃላ ፍትህ እንድታገኝ የክልሉ መንግስት አበክሮ ይሰራል ነው ያሉት። 

ወይዘሪት ፀጋ በላቸውን ከተጠርጣሪ ግለሰብ ለማስጣል በተደረገው ጥረት የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት፣ የፌዴራል ፖሊስ፣ የክልሉ የጸጥታ ሀይልና ሕዝቡ ላደረጉት ጥረት አመስግነዋል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም