በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 27ኛ ሳምንት ዛሬ ሁለት ጨዋታዎች ይካሄዳሉ

321

አዲስ አበባ ግንቦት 25/2015 (ኢዜአ):- በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ27ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር የሁለተኛ ቀን ውሎ ሁለት ጨዋታዎች በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይደረጋሉ።

በመርሐ-ግብሩ መሰረት ሃዋሳ ከተማ ከወላይታ ድቻ ከቀኑ 7 ሰአት ላይ ይጫወታሉ።

በደረጃ ሰንጠረዡ ሃዋሳ ከተማ በ35 ነጥብ 8ኛ ላይ የተቀመጠ ሲሆን ወላይታ ድቻ በአንጻሩ በ33 ነጥብ 12ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ሃዋሳ ከተማ በፕሪሚየር ሊጉ ከ19ኛ ሳምንት በኋላ ባሉ ሰባት ጨዋታዎች ማሸነፍ አልቻለም።

በፕሪሚየር ሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች አንድ ጊዜ ሲሸነፍ አራት ጊዜ ነጥብ ተጋርቷል።

ተጋጣሚው ወላይታ ድቻ በአንጻሩ ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው አንድ ጊዜ ብቻ ነው፤ በሶስቱ አቻ ሲወጣ በአንዱ ተሸንፏል።

ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያው ዙር 11ኛ ሳምንት ያደረጉት ጨዋታ አንድ አቻ መለያየታቸው የሚታወስ ነው።

ሌላኛው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ27ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር ድሬዳዋ ከተማ እና አዳማ ከተማን ከቀኑ 10 ሰአት ላይ ያገናኛል።

ድሬዳዋ ከተማ በ36 ነጥብ 7ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠ ሲሆን አዳማ ከተማ በ33 ነጥብ 11ኛ ደረጃን ይዟል።

ድሬዳዋ ከተማ በፕሪሚየር ሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች ሶስቱን ሲያሸንፍ በሁለቱ ተሸንፏል።

ተጋጣሚው አዳማ ከተማ ደግሞ ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ማሸነፍ አልቻለም፤  በሶስቱ ነጥብ ሲጋራ ሁለት ጊዜ ደግሞ ተሸንፏል።

ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያው ዙር በ13ኛ ሳምንት ባደረጉት ጨዋታ አዳማ ከተማ 2 ለ 0 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።

በተያያዘም ትናንት በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ27ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ጨዋታዎች የሊጉ መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ ለገጣፎ ለገዳዲን 2 ለ 1 ሲያሸንፍ ሲዳማ ቡና ከአርባ ምንጭ ከተማ አንድ አቻ ተለያይተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም