በኢጋድ ቀጣና ዘላቂ ሰላም እና መረጋጋት እንዲፈጠር በሚደረገው ጥረት ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ጉልህ ድርሻ አላቸው--አምባሳደር መለስ ዓለም

265

አዲስ አበባ ግንቦት 25/2015(ኢዜአ):-በምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ቀጣና ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት እንዲፈጠር በሚደረገው ጥረት የመገናኛ ብዙኃን ሚና የላቀ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም ገለፁ።

አምባሳደር መለስ ይህን የገለፁት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከኢጋድ ጋር በመተባበር የፀጥታ እና ደህንነት ጉዳዮች ዘገባዎች እና የመገናኛ ብዙኃን ሚና በሚል ከተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ለተውጣጡ ጋዜጠኞች በተዘጋጀ ሥልጠና ላይ ነው።

ቃል አቀባዩ "ለዘላቂ ሰላም እና መረጋጋት የመገናኛ ብዙኃን ሚና" በሚል የመነሻ ጽሑፍ አቅርበዋል።

አምባሳደር መለስ የመገናኛ ብዙኃን በኢጋድ እንደ ቀጣና እና እንደ አገር በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እና መረጋጋት ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው የዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን በማቅረብ አብራርተዋል።

የሰላም እና ፀጥታ ጉዳዮች ምሁሩ ዶክተር ዮናስ አዳዬ የኢጋድ ቀጣና ወቅታዊ የጂኦ ፖለቲካ አዝማሚያ ላይ ያተኮረ ማብራሪያ አቅርበዋል።

ዶክተር ዮናስ በገለፃቸው የአፍሪካ ቀንድ የተለያዩ ፍላጎቶች ከሚንፀባረቁባቸው ቀጣናዎች መካከል አንዱ መሆኑን አንስተዋል።


 

መገናኛ ብዙኃን መረጃዎችን ለሕዝብ ከማድረሳቸው አስቀድመው የቀጣናውን ትክክለኛ ገፅታ ከተለያዩ መመዘኛዎች አንፃር መፈተሽ እንዳለባቸው አብራርተዋል።

በኢጋድ ክልል ውስጥ የግጭት እና የፀጥታ ጉዳዮች ተፈጥሮ እና ተለዋዋጭነት እንዲሁም በኢትዮጵያ የድህረ ግጭት የሰላም ግንባታን በሚመለከትም ዶክተር ዮናስ ገለፃ አድርገዋል።

የሥልጠናው ተሳታፊዎችም የተለያዩ ጥያቄዎች እና አስተያየቶችን በማንሳት ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል።

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም