ዩኒቨርሲቲዎች አገር በቀል እውቀቶችን ከዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች ጋር በማስተሳሰር ለአገር ግንባታ ማዋል እንዳለባቸው ተገለጸ

ደብረ ብርሃን ግንቦት 24/2015 (ኢዜአ):-  የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አገር በቀል እውቀቶችን ከዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች ጋር በማስተሳሰር ለአገር ኢኮኖሚ ግንባታ እና ለችግሮች መፍቻ ማዋል እንደሚገባ ተጠቆመ። 

በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ "የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሳምንት ቀን" በተለያዩ ዝግጅቶች በመከበር ላይ ነው።

የኢትዮጵያ ባዮ እና ኢመርጂንግ ቴክኖሎጂ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ካሳሁን ተስፋዬ እንዳሉት፣ የአገር ኢኮኖሚን ለመገንባት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በምርምር የታገዘ ድጋፍ ማድረግ አለባቸው። 

ተቋማቸው የአገር ኢኮኖሚ በጽኑ መሰረት ላይ እንዲቀመጥ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች በምርምር እንዲወጡና  ለተጠቃሚዎች እንዲደርሱ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
 

ከደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በሲዳማ ክልል ይርጋለም ከተማ የቡና ገለባን ወደ ማዳበሪያ ለመቀየር ያከናወነው ስራ ውጤታማ ሆኖ በመገኘቱ ቴክኖሎጂውን ለአርሶ አደሮች እንዲሸጋጋር መደረጉን ተናግረዋል።

እንዲሁም የቲማቲም በሽታን በመከላከል የዘርፉን ምርታማት ለማሳደግ ከኬሚካል ነጻ የሆነ የተባይ መከላከያ መድሀኒት ተቋሙ በምርምር ማውጣቱን ነው የገለጹት።

ከእዚህ በተጨማሪ የማሽላ ጥንቅሽ ዝርያን ለፋርማሲዩቲካልና ለምግብነት አገልግሎት ለማዋል ከመልካሳ ግብርና ምርምር ጋር ውጤታማ ስራ መሰራቱን ነው ዶክተር ካሳሁን የተናገሩት።

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አገር በቀል እውቀቶችን ከመጠበቅ ባለፈ ከአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ጋር በማስተሳሰር አገራዊ ችግሮችን ለመፍታትና ለኢኮኖሚ ግንባታ ማዋል እንዳለባቸው አሳስበው ተቋሙ ለዚሁ ስራ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አመልክተዋል።

የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ጥናትና ምርምር የማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር አዝመራ አየሁ በበኩላቸው፣ በዩኒቨርሲቲው ችግር ፈች የምርምር ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አመልክተዋል።
 

ለዚህም በግብርናው ዘርፍ የተቀናጀ የአሳ እርባታ፣የኮምፖስት ዝግጅት እንዲሁም የአንኮበር የመድኃኒት እጽዋት ምርምሮች ውጤታማ እየሆኑ መምጣታቸውን በማሳየነት ጠቅሰዋል።

ከኢንዱስትሪ ባለሀብቶች ጋር በመቀናጀት የኢንዱስትሪ ዩኒቨርሲቲ ትስስርን ለማጠናከር ጅምር ሥራዎች እንዳሉም አንስተዋል። 

እንደ አገር ዘላቂ ልማት ለማረጋገጥ በሚደረጉ ጥረቶች ዩኒቨርሲቲው ብቁ እና ተወዳዳሪ የሰው ኃይል በማፍራት የድርሻውን እየተወጣ ነው መሆኑን ነው ምክትል ፕሬዝዳንቱ የተናገሩት።

በዚሁ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሳምንት ቀን የተለያዩ ባለድርሻ አካላትና ተማሪዎች እንዲሁም አምራች ኢንዱስትሪዎችና ተመራማሪዎች ተሳታፊ ሆነዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም