በኢትዮጵያ የኪነጥበብ ኢንዱስትሪው ለሀገር ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ያለውን ሚና ለማሳደግ ቅንጅታዊ አሰራርን ማጠናከር ይገባል-የኪነጥበብ ባለሙያዎች

163

አዲስ አበባ ግንቦት 24/ 2015 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ የኪነ ጥበብ ኢንዱስትሪው ለሀገር ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ያለውን ሚና ለማሳደግ ቅንጅታዊ አሰራርን ማጠናከር እንደሚገባ  የዘርፉ ባለሙያዎች ገለጹ።

የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ከስራና ክህሎት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የኪነ-ጥበብና ስነ-ጥበብ ፈጠራን ለማሳደግ የሚያስችል የባለድርሻ አካላት የውይይት መድረክ ተካሂዷል።

በውይይቱ በኪነጥበብና ስነ ጥበብ የስራ እድል ፈጠራ ዙሪያ የመወያያ የመነሻ ጽሁፍ ያቀረቡት በስራና ክህሎት ሚኒስቴር የማኑፋከቸሪንግ ልማት ባለሙያ አቶ በኃይሉ ዓለማየሁ፤ የጥበብ ኢንዱስትሪ ለሀገር ኢኮኖሚ ዕድገትና ለዜጎች የስራ እድል በመፍጠር ረገድ እምቅ አቅም ያለው ዘርፍ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ፈርጀ ብዙ የባህል ኪነጥበብ ቢኖራትም በሚፈለገው ልክ ባለማደጉ ለሀገር ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ያለው አበርክቶ አነስተኛ ሆኖ መቆየቱን ጠቅሰዋል።

ሆኖም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ዘርፉ እየተነቃቃ መምጣቱን በማንሳት በዚህም በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ያለው ድርሻ እየጨመረ መምጣቱን ነው የገለጹት።

አቶ በኃይሉ የናይጄሪያ የፊልምና የሙዚቃ ኢንዱስትሪ  በስራ እድል ፈጠራ ያለውን ትልቅ ሚና በተሞክሮነት ጠቅሰው፤ የውጭ ምንዛሬ በማስገባት ከነዳጅ ቀጥሎ ትልቁ የገቢ ምንጭ መሆኑን አስረድተዋል።

ከሌሎች ሀገራት ተሞክሮ በመማር የኢትዮጵያን የኪነጥበብ ኢንዱስትሪ በማጎልበት ለሀገር ልማትና ለዜጎች ተጠቃሚነት ጉልህ አስተዋፅኦ እንዲያበረክት በቅንጅት መስራት ተገቢ መሆኑን አንስተዋል።

የጥበብ ስራዎች ቅጅና ተዛማጅ መብቶች ዙሪያ የመወያያ ሀሳብ ያቀረቡት የሰዋሰው መልቲ ሚዲያ ጥናትና ምርምር ከፍተኛ ባለሙያ ታደሰ ኃይሉ በበኩላቸው፤ ሀገሪቱ ያላትን ዘርፈ ብዙ ባህልና እውቀቶች ለማሳደግና ተጠቃሚ ለመሆን የቅጅና ተዛማጅ መብቶች መከበር አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።

በቀጣይ ፈጠራን ለማሳደግና የሀገርን የቅጂ መብት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ባለስልጣንን ጨምሮ ሌሎች ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ ነው ያመለከቱት።

የሙዚቃ ባለሙያው ዳዊት ይፍሩ በበኩሉ፤ በነባርና አዳዲስ የኪነጥበብ ባለሙያዎች የፈጠራ ስራቸው የቅጂ መብት ስጋቶች እንዳሉ በመጠቆም፤ አዳዲስና የተሻሉ የኪነጥበብ ፈጠራ ስራዎችን ለማውጣት የቅጂና ተዛማጅ መብቶችን ማረጋገጥ ላይ ላይ በትኩረት እንዲሰራ ጠይቋል።

በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የዕደ ጥበብ ልማትና ገበያ ትስስር ማስፋፊያ ስራ አስፈጻሚ አቶ ነጋሽ በድሩ፤ መንግስት የኪነጥበብ ዘርፉን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ሚና ለማሳደግ እየሰራ ነው ብለዋል።

የአማራ ክልል ስራና ስልጠና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አወቀ ዘመነ፤ በኢኮኖሚ ያደጉ ሀገራት ለአዕምሮዊ ሃብት ጥበቃ ትልቅ ትኩረት እንደሚሰጡ  ጠቅሰዋል።

በኢትዮጵያም ያልተነካውን የባህልና የጥበብ ዘርፍ ለማሳደግ በቁርጠኝነት መስራት ከሁሉም የሚጠበቅ ኃላፊነት መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም