በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በክረምቱ ከ50 ሺህ በላይ ወጣቶችን ያሳተፈ የክረምት በጎ ፈቃድ ስራዎች ይከናወናሉ- ቢሮው

167

አሶሳ ግንቦት  24 / 2015(ኢዜአ)፡-  በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በመጪው ክረምት ከ50 ሺህ በላይ ወጣቶች የሚሳተፉበት የክረምት በጎ ፈቃድ ስራዎች እንደሚከናወኑ የክልሉ ሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ አስታወቀ፡፡

በክልሉ የሻንጉል በጎ አድራጎት ማህበር በበኩሉ፤ ባለፉት ወራት ያከወናቸውን በጎ ተግባራት በመጪው ክረምትም አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጿል፡፡

የቢሮው ሃላፊ ወይዘሮ ሃጂራ ኢብራሂም ለኢዜአ እንዳሉት፤  ከመጪው ሐምሌ   ጀምሮ ለሶስት ተከታታይ ወራት  የክረምት በጎ ፈቃድ ስራዎች ለማከናወን አቅደዋል።

በእቅዳቸው መሰረት  በግል እና በማህበር የተደራጁ ከ50 ሺህ በላይ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ተሳታፊ እንደሚሆኑ አስታውቀዋል፡፡

በበጎ ፈቃድ ስራ ክልሉን ብሎም የሃገሪቱን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማጎልበት የሚከናወኑ ስራዎች መለየታቸውን ጠቁመዋል፡፡

ከመካከላቸውም ባለፉት ዓመታት የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መረሃ ግብር   በክልሉ አጠናክሮ ለማስቀጠል የሚካሄድ ችግኝ ተከላና እንክብካቤ ዋነኛው እንደሆነ ወይዘሮ ሃጂራ ጠቅሰዋል፡፡

እንዲሁም አቅመ ደካሞችን የመርዳት ፣ የክረምት ትምህርት ማጠናከሪያ፣ የአካባቢ ጽዳትና  ህገወጥ የሰዎች ዝውውር መከላከል ከሚከናወኑት ተግባራት መካከል  እንደሚገኙበት አመላክተዋል፡፡ 

በበጎ ፈቃድ ስራው የሚሳተፉ ወጣቶች በተጨማሪ በሚያከናውኗቸው ስራዎች ህብረተሰቡን ከመደገፍ ባሻገር የህይወት ተሞክሮዎች እንደሚቀስሙበት ጠቁመዋል፡፡

ባለፈው የበጋ ወቅት በተለይም ወጣቶች ከጸጥታ አስከባሪዎች ጎን በመቆም ለክልሉ ሠላም መመለስ ያደረጉት አስተዋጽኦ የሚበረታቱ መሆናቸውን አውስተዋል፡፡

ሆኖም  የወጣቶች ማህበራትን ከመደገፍ ጀምሮ የተደረው ጥረት አነስተኛ መሆኑን አመልክተው፤ ይህም በበጋው የበጎ ፈቃድ ስራ የቢሮው ዋነኛ ውስንነት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ውስንነቶችን  ለማስተካከል በክረምቱ ልዩ ትኩረት እንደሚሰጥ ወይዘሮ ሃጂራ ገልጸዋል፡፡

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከሚገኙ የበጎ አድራት ወጣቶች ማህበራት መካከል  14 አባላትን የቀፈው የሻንጉል በጎ አድራጎት ማህበር አንዱ ነው፡፡


 

ማህበሩ ለትርፍ ያልተቋቋመና ዓላማው የተጎዱ ወገኖችን በመርዳት የሃገር ገጽታ መገንባት መሆኑን የማህበሩ ስራ አስኪያጅ ወጣት ፌኔት አያና ተናግራለች፡፡

በክልሉ በርካታ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ወገኖች አሉ ያለችው ወጣቷ፤ ከህብረተሰቡ የድጋፍ ገንዘብ በማሰባሰብ ለችግረኛ ወገኖች አነስተኛ መኖሪያ ቤት አሰርተው በመስጠት ባለፉት ወራት ካከናወኗቸው ተግባራት መካከል መሆኑን አስረድታለች፡፡

በመጪው ክረምትም ይኸው የበጎ ተግባር ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጠል ወጣቷ ገልጻለች፡፡

የማህበሩ አባል ወጣት ወይንእሸት ደሳለኝ በሰጠችው አስተያየት፤ ለበጎ ፈቃድ ስራው የምናውለውን ገንዘብና ሌሎች የቁሳቁስ ድጋፎችን ከህብረተሰቡ ለማሰባሰብ ማህበራዊ ሚዲያን እየተጠቀምንበት ነው ብላለች፡፡

በበጎ ፈቃደኝነት የሚከናወኑ ተግባራት በምንም የማይተመን የህሊና እርካታ የሚሰጥ እንደሆነም ወጣቷ ለኢዜአ ገልጻለች፡፡

በሻንጉል በጎ አድራጎት ማህበር ወጣቶች የበጎ ፈቃድ የወደቀ ቤታቸው ተጠግኖ  ለአገልግሎት መብቃቱን የተናገሩት ደግሞ  አቶ ብርሃኑ ኪሮስ የተባሉ የአሶሳ ከተማ ነዋሪ ናቸው።

በተደረገላቸው ድጋፍ  ደስተኛ እንደሆኑና ለዚህም ምስጋና አቅርበዋል፡፡

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ባለፈው ዓመት  215 ሺህ 432 ሰዎችን ተጠቃሚ ያደረጉ ከአራት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ የበጎ ፈቃድ ስራዎች መከናወናቸውን ከቢሮው የተገኘው መረጃ አመልክቷል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም